ዮጵያ ነገ ዜና፡– የዓለም ኃያሏ ሀገር አሜሪካ በኮሮና ቫይረስ የሞቱባት ዜጎች ቁጥር በቬትናም፣ በኢራቅ፣ በአፍጋኒስታንና በኮሪያ ጦርነቶች በድምሩ ከሞቱትም በላይ ነው ተባለ።
በሀገሪቱ የሟቾች ቁጥር ከመቶ ሺኅ ሲበልጥ፤ ጠቅላላው የዓለም የሟቾች ቁጥር ደግሞ 354 ሺኅ 984 እንደደረሰ ታውቋል።
በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ በዓለም ላይ ያሉ አኃዞችን እየተከታተለ ይፋ የሚያደርገው የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የመረጃ ቋት እንደሚያሳየው ከሆነ፤ አሁን ላይ በትክክል በአሜሪካ ምድር የተመዘገው የሟቾች ቁጥር 100 ሺኅ 276 ደርሷል፡፡
ዓለምን በእጅጉ ያስገረመው ይህንን የአሜሪካን እልቂት የቢቢሲው የሰሜን አሜሪካ የፖለቲካ አርታኢ ጆን ሶፔል፤ “አሜሪካ አሁን በኮቪድ-19 ያጣቻቸው ዜጎቿ ቁጥር በታላቁ የቬትናም ጦርነት፣ በኢራቅ፣ በኮሪያ፣ በአፍጋኒስታን ባለፉት 44 ዓመታት የሞቱባት ዜጎች ተደምረው እንኳ የሚበልጥ ነው” ሲል ይገልፀዋል።
የአሜሪካው የበሽታ መቆጣጠር እና መከላከያ ማዕከል-ሲዲሲ በአገሪቱ በቫይረሱ ሳቢያ የሞቱ ሰዎች ቁጥርን በእድሜ ከፋፍሎ ባወጣው ዝርዝር መሠረት አብዛኛዎቹ ሟቾች እድሜያቸው ከ85 ዓመት በላይ ሲሆኑ፤ ኒው ዮርክ፣ ኒው ጀርሲ እና ማሳቹሴት ግዛቶች ደግሞ በርካታ ሰዎች የሞቱባቸው ቀዳሚ የአሜሪካ ግዛቶች ሆነው ተመዝግበዋል።
በሌላ በኩል ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ይፋ ባደረገው አኃዝ መሰረት፤ በብራዚል 15 በመቶ የኮቪድ-19 ሟቾች እድሜያቸው ከ50 ዓመት በታች ፣በሜክሲኮ ደግሞ 25 በመቶ የሚሆኑት ከ25 እስከ 49 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ፤ በዚህ ወቅት በመላው ዓለም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም አምስት ሚሊየን ስድስት መቶ ሺኅ ደርሷል።