ዛሬ ማለዳ በጋሞ ዞን በተከሰተ የመሬት ናዳ የ10 ሰዎች ሕይወት አለፈ

ዛሬ ማለዳ በጋሞ ዞን በተከሰተ የመሬት ናዳ የ10 ሰዎች ሕይወት አለፈ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በደቡብ ክልል ጋጮባባ በተሰኘ ወረዳ “ጋፀ ” እና “ግና” በሚባሉ ሁለት ቀበሌዎች ውስጥ በተከሰተ የመሬት ናዳ የ10 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተሰማ።

አደጋው ዛሬ ጠዋት የጣለውን  ከባድ ዝናብ ተከትሎ መከሰቱን የገለጹት የዞኑ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ረታ ተክሉ፤ በአደጋዉ ከሞቱት ሰዎች መካከል የስድስቱ አስከሬን መገኘቱን፣ የቀሪዎቹን አራት ሰዎች አስከሬን በሰው ኃይል ቁፋሮ ለማግኘት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
አደጋው የተከሰተበት ቦታ ተራራማ በመሆኑና የመኪናው መንገድ በናዳ የተዘጋ ስለሆነ ፍለጋውን የሚያፋጥን ዶዘር ማስገባት አለመቻሉም ታውቋል።
“የጋሞ ዞን ፀጥታ ኃይሎችና የአመራር አካላት በእግር ተጉዘው በሥፍራው በመድረስ ኅብረተሰቡን በማስተባበር ላይ ይገኛሉ” ያሉት የፖሊስ አመራር፤ በአደጋው የተፈናቀሉ ሰዎች ብዛትና የንብረት ውድመት መረጃ እየተጣራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
በጋሞ ዞን የተለያዮ ስፍራዎች ዛሬ ማለዳ የጣለውን ዝናብ ተከትሎ የደረሰውን የመሬት መናድ ሳይጨምር፤ በያዝነዉ ዓመት ብቻ በአካባቢው በተከሰተ የመሬት ናዳ 12 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

LEAVE A REPLY