ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ከተጠበቀውና ከተገመተው በታች በእጅጉ የወረደ ገንዘብ ያሰባሰበው የአዲስ አበባ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት፣ የህዳሴ ምክር ቤት በአዲስ መልክ ሊደራጅ ነው።
በዋና ከተማዋ ሰፊ የሕዝብ ንቅናቄ መድረክ መፍጠርም ሆነ አጥጋቢ ሥራ መሥራት አልቻለም የተባለውን የህዳሴውን ምክር ቤት በልዮ ሁኔታ ለማዋቀር ዛሬ ውይይት ተደርጓል።
በግድቡ ዙሪያ በአዲስ አበባ ከተማ ያለው ሕዝባዊ ተሳትፎ መቀዛቀዙን መነሻ በማድረግ ጽ/ቤቱን በአዲስ መልክ ማዋቀር አስፈላጊ መሆኑን የገለፁት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር እንዳወቅ አብቴ ፤ ዳግም በተሻሻለ መንገድ የሚቋቋመው ምክር ቤት ሓላፊነት፣ ተግባራት እና አጠቃላይ የሥራ አፈፃፀም በውይይቱ መቋጫ ላይ እንደሚገለፅ አስታውቀዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ በውይይት መድረኩ ላይ በህዳሴ ግድቡ ግንባታ ፕሮጀክት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኢ/ር ኤፍሬም ወ/ኪዳን ዝርዝር ሪፖርት ከማቅረባቸው ባሻገር፣ በ2013 ዓ.ም መጨረሻ ኃይል ለማመንጨት ዕቅድ መነደፉንም አስታውቀዋል፡፡
ቀደም ሲል በነበረው የከተማው የህዳሴው ምክር ቤት አማካይነት በ2012 በጀት ዓመት 550 ሺኅ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ፤ 100 ሚሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ ከ 756 ሺኅ 859 የኅብረተሰብ ክፍሎች የተሰበሰበው ገንዘብ ግን 7 ሚሊየን 333 ሺኀ 184 ብር ከ 93 ሳንቲም ብቻ መሆኑ ታውቋል፡፡
ይህ በጣም የወረደ ገንዘብ ሥራውን በአግባቡ ማከናወን ያቃተው ምክር ቤት በአዲስ መልክ እንዲዋቀር አድርጎታል።