ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ግንቦት 20 የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ያስከበረ ነው ተብሎ በብሔራዊ የድል በዓልነት መከበር የለበትም ሲሉ አቶ ኦባንግ ሜቶ ገለፁ።
በግንቦት 20 ድል ድልድዮችና መንገዶች ቢሰሩም የኢትዮጵያዊነት ፍቅር፣ ሰላምና አንድነት መንገዶች ግን እንዲፈርሱ ብዙ ተለፍቶበታል ሲሉም የህወሓት/ኢሕአዴግ የድል ቀን ይዞት ከመጣው ትሩፋት የተከለው ክፉ ነቀርሳ እንደሚበልጥ አስረድተዋል።
ግንቦት 20 ብዙ ጊዜ የሚወሳበት የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት ሲወራ የነበረውን ያክል አልተተገበረም ያሉት የሰብኣዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶ፤ “ቀኑ ኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማምጣት ባደረጉት ትግል የተገኘ ውጤት ቢሆንም ፤ ከመነሻው ጀምሮ ለሥልጣንና ለውስን ሰዎች ጥቅም የቆመ፣ የራሱ የሆነ ድብቅ ዓላማ ነበረው” ሲሉም ላለፉት 27 ዓመታት ሥልጣን ላይ የተቀመጠው ፓርቲ ለድል የበቃበትን ሂደት አጣጥለዋል።
ህወሓት/ ኢሕአዴግ አገሪቱን ያስተዳድር በነበረበት ወቅት ኢትዮጵያዊነትና በሰላም አብሮ መኖር እሴቶች በከፍተኛ ደረጃ የተሸረሸረበት፣ ሙስና የተስፋፋበት፣ የሰብዓዊ መብት በከፋ መልኩ የተጣሰበት ወቅት እንደነበር ያስታወሱት የሰብኣዊ መብት ተሟጋቹ፤ ግንቦት 20 ከሁለት ዐሥርት ዓመታት በላይ በሕዝብ ሥም እየተማለ የተነገደበት፣ ብዙዎች የተገደሉበት፣ የተኮላሹበትና አካላቸው የጎደለበት ቀን ነው ብለውታል።
“በዚህ ሂደት ውስጥ እኩልነታቸው ተጠብቋል የሚባሉ ካሉም የሥርዓቱ አገልጋዮችና በሥልጣን ላይ የነበሩ ጥቂቶች ብቻ ናቸው” ሲሉ የተናገሩት አቶ ኦባንግ ሜቶ፤ ክልሎችም ቢሆኑ በነፃነት ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ እንዳልነበር፣ የሚገባቸውንም ጥቅም ሲያገኙ እንዳልቆዮ፣ በተለይም እንደ ጋምቤላ ያሉ ታዳጊ ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ሥልጣናቸውን ተነጥቀው በተግባር የሚያስተዳድራቸው ሌላ አካል ነበር” በማለት ግንቦት 20 ለብሔር ብሔረሰቦች የፈየደው ነገር እንደሌለ አመላክተዋል።