ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የጤና ኮሌጅ የሁለተኛ ድግሪ ተማሪ የነበረችው እና ግንቦት 17 ቀን 2012 ዓ/ም በኮሌጁ አስተዳደር ህንፃ ላይ በሚገኘው የላቦራቶሪ ቤተ ሙከራ ክፍል ውስጥ ሞታ የተገኘችው የሃይማኖት በዳዳ ገዳይ በቁጥጥር ስር ዋለ።
የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ የሆነውና በ20ዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ደግነት ወርቁ የተባለ ወጣት የ27 ዓመቷን ሃይማኖት በዳዳ ሕይወት ያጠፋ መሆኑን አረጋግጫለሁ ያለው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፤ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት ጋር በመሆን ቀን ከሌሊት ባካሄደው ክትትል ግለሰቡን ትናንት ምሽት አንድ ሰዐት ላይ እንደያዘው ይፋ አድርጓል።
ወጣቱ የ12ኛ ክፍል ተማሪ እንደነበር፣ “የኤች አይ ቪ ኤድስ መድኃኒት ለማግኘት ምርምር ላይ ስለሆንኩ የጥቁር አንበሳ ሐኪሞች ይርዱኝ’ በማለት ወደ ግቢው በተለያዩ ጊዜያት ይመላለስ እንደነበር የገለፀ ሲሆን፤ ከሟች ጋር ምንም ዓይነት ትውውቅ እንዳልነበራቸው ትናንት እስከ እኩለ ሌሊት በተደረገ ምርመራ የወንጀሉን ዝርዝር ለፖሊስ አስረድቷል።
የሕክምና ተማሪዋ በተገደለችበት ቀን እንደ ልማዱ ለዚሁ ጉዳይ እንደመጣ፣ ገንዘብ እንደተቸገረና ቢላዋ ይዞ በግቢው ውስጥ ከሚገኙ ቢሮዎች በአንዱ ላፕቶፕ ወይም ሞባይል ካገኘ ሰርቆ ሽጦ ለመጠቀም ሲዟዟር የሟች ክፍል ክፍት ሆኖ በማግኘቱ መግባቱንም ግለሰቡ በሰጠው እማኝነት አረጋግጧል።
በመጀመሪያ ድግሪ ከቴፒ ዩኒቨርስቲ በማዕረግ ተመርቃ በዩኒቨርስቲው ስታገለግል የቆየችው ሃይማኖት በዳዳ፤ ለተጨማሪ ትምህርት ወደ ጥቁር አንበሳ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተልካ ትምህርቷን በመከታተል ላይ ሳለች በኮሌጁ አስተዳደር ህንፃ ላይ በሚገኘው የላቦራቶሪ ቤተ ሙከራ ክፍል የሰውነት ክፍሏ በአሰቃቂ ሁኔታ በስለት ተወግቶ፣ በማግስቱ ከቀኑ 11 ሰዓት አስከሬኗ በክፍሉ ውስጥ መገኘቱ ይታወቃል።