ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የሼህ ሆጀሌ አል ሀሰን ኡመድ የአዲስ አበባ ማረፊያ የነበረው ታሪካዊ የመኖሪያ ሕንፃ ቅርስን ለማደስ የ10 ሚሊዮን ብር በጀት እንደሚፀድቅለት ተነገረ።
በተለምዶ ሩፋኤል አካባቢ የሚገኘውና የበርታ ብሔረሰብ ገዥ የነበሩት ሼህ ሆጀሌ አል ሀሰን ኡመድ የአዲስ አበባ መቆያ በነበረው ቤት ይኖሩ ለነበሩ ሰዎች እድሳቱን፣ እንዲሁም ቅርስነቱን ተከትል ሌላ የተገነባ መኖሪያ እንዲያገኙ እንደሚደረግም ታውቋል።
ቅርሱን ለማደስ፣ ታሪካዊነቱን ለመዘከር የከተማ መስተዳድሩ የ10 ሚሊዮን ብር በጀት ያፀድቅለታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከከተማ አስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
አሁን ላይ ታላቁ ሰው በስማቸው ከሚጠራው መስጂድ አቅራቢያ የሚገኘው ይኸው መኖሪያ፣ ሼህ ሆጀሌ አልሀሰን ኡመድ በአፄ ምንሊክ ዘመን ለንጉሠ ነገሥቱ ልዩ ልዩ ስጦታዎችን ይዘው፣ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ያርፉበት የነበረ ቤት ነው።