ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ የተገኘባት የአዲስ አበባ ከተማዋ ልደታ፣ ለእንቅስቃሴ ዝግ በሆነው አብነት አካባቢና በአዲስ ከተማ ከፍለ ከተማ ለሚገኙ 1 ሺኅ ለአደጋ ተጋላጭ ናቸው ለተባሉ ነዋሪዎች የምግብ ድጋፍ ተደረገ።
ለሦስት ወራት የሚቆየውን የምግብ አቅርቦቱን የደገፈው ቢልጌትስ ፋውንዴሽን እንደሆነም ታውቋል።
በከተማዋ ለሚገኙ ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ ማኅበረሰብ አባላት የሚደረገውን የምግብ አቅርቦቱን ያስጀመሩት የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ፤ ከኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር መጨመር ጋር በተያያዘ በሚከሰቱ ችግሮች ብዙዎች ችግር ውስጥ ሊወድቁ ስለሚችሉ ከመንግሥት ድጋፍ ባለፈ እርስ በእርስ መረዳዳት የሚያስፈልግበት ወሳኝ ጊዜ ላይ መደረሱን ተናግረዋል።
የምግብ አቅርቦቱ በየሁለት ቀኑ ለነዋሪዎቹ የሚከፋፈል መሆኑን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።