ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የጀርመን መንግሥት ለኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ 4 ዘመናዊ አውቶብሶችን ድጋፍ ማድረጉ ተነገረ።
የሁለቱ ሀገራት የፖሊስ ተቋማትም የወንጀል መከላከል፣ የወንጀል ምርመራ፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በመከላከልና መረጃን በመለዋወጥ እንዲሁም በፖሊስ ሳይንስ ትምህርትና ሥልጠና በጋራ ይሠራሉ፡፡
የጀርመን ፌደራል ፖሊስ ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በተለያዩ ጊዜያትም ድጋፎችን ያደረገ ሲሆን፤ በትላንትናው ዕለትም ሁለት 63 ሰው የመጫን አቅም ያላቸው እና ሁለት 29 ሰው የመጫን አቅም ያላቸው በጥቀሉ 4 ዘመናዊ አውቶብሶችን ለኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ድጋፍ አድርጓል፡፡
በኢትዮጵያ ተሰናባቿ የጀርመን አምባሳደር ብሪት ቫይነር የአውቶብሶችን ቁልፍ ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው ባስረከቡበት ወቅት፤ ጀርመንና ኢትዮጵያ ያላቸውን የረጅም ዘመን ጠንካራ ግንኙነትን አስታውሰው የአውቶብሶቹ ድጋፍ የሁለቱ ሃገራት መንግሥታትና የፖሊስ ተቋማት ጠንካራ ግንኙነት ማሳያ ነውም ብለዋል።
ኮሚሽነር ጀነራል እንዳሻው ጣሰው በበኩላቸው በጀርመን መንግሥት የተደረገው ድጋፍ ተቋሙ እየተገበረ ባለው የለውጥ ሥራ ላይ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር በመሆኑ ለተደረገው ትብብር ምስጋና አቅርበዋል።
ከጀርመን መንግሥት የተደረገው ድጋፍ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ የሚሠራውን ዘርፈ ብዙ ተግባር የተቀላጠፈ በማድረግ በኩል ከፍተኛ አስተዋፆኦ እንደሚኖረው ተነግሮለታል።