ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በሚኒያ ፖሊስ ያልታጠቀ ጥቁር አሜሪካዊ፣ በነጭ ፖሊስ ከተገደለ በኋላ፤ ለግድያው ፍትህ የሚጠይቁ አሜሪካያን በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ከፖሊስ ጋር የሚያደርጉት ግጭት ቀጥሏል።
የጆርጅ ፍሎይድን ግድያ ለመቃውም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ትናንት ምሽት ዋይት ሃውስ ፊት ለፊት የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጋቸውን ተከትሎ፤ ባለሥልጣናት አካባቢውን ከእንቅስቃሴ ውጪ በማድረግ በፍጥነት አዘግተውታል።
ሚኒሶታ፣ ኒው ዮርክ፣ አትላንታ፣ ቴክሳስ እና ሌሎች ግዛቶችም አመጽ የተሞላበት የተቃውሞ ሰልፎችን ያስተናገዱ ከተሞች ሆነዋል።
ለጆርጅ ፍሎይድ ሞት ተጠያቂ ነው የተባለው የቀድሞ የሚኒያፖሊስ ከተማ የፖሊስ ባልደረባ የግድያ ክስ እንደተመሰረተበት እየተነገረ ነው።
የጆርጅ ፍሎይድ ገዳይ በመሆን የተጠረጠረው፣ ዴሪክ ቹቪያን የተባለው 44 ዓመት ፖሊስ የፊታችን ሰኞ ፍርድ ቤት ይቀርባል ተብሏል።
በተቀጣጣለው አመፅ ሚኒሶታ ከየትኛውም ግዛት በበለጠ ከፍተኛ ተቃውሞ ያስተናገደች ግዛት ሆናለች። በሚኒያ ፖሊስ-ሴንት ፖል ሰዐት እላፊ ቢታወጅም፤ ሰልፈኞች የሰዐት እላፊ አዋጁን ወደ ጎን በመተው ፖሊስ ጣቢያዎችን እና የፖሊስ ተሽከርካሪዎችን በእሳት አጋይተዋል።
ግርግሩን በመጠቀም ዘረፋ የሚፈጽሙም በመብዛታቸው፣ የከተማዋ ፖሊስ የተቀሰቀሱ አመጾችን መቆጣጠር የተሳነው በመሆኑ፤ ፔንታጎን በሚኒያ ፖሊስ የአገሪቱ ጦር ሊሠማራ ይችላል ሲል ጠቁሟል።
በአትላንታ ህዝብ እና ንብረት ለመጠበቅ በሚል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀ ሲሆን፤ በኒው ዮርክ ግዛት ብሩክሊን አካባቢም በተመሳሳይ ሁኔታ የተቃውሞ ሰልፉ ወደ አመጽ ተቀይሮ ሰልፈኞች የፖሊስ ተሽከርካሪዎችን አውድመዋል።