ከመስከረም 30 በኋላ መንግሥት የለም ለሚሉ ጽንፈኞች የኦሮሚያ ክልል ማስጠንቀቂያ ሰጠ

ከመስከረም 30 በኋላ መንግሥት የለም ለሚሉ ጽንፈኞች የኦሮሚያ ክልል ማስጠንቀቂያ ሰጠ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ከመስከረም 30 በኋላ መንግሥት የለም በማለት ብጥብጥ ለማንሳት መንቀሳቀስ ተቀባይነት የለውም ሲል የኦሮሚያ ክልል መንግሥት አስታወቀ።

“ወረርሽኝ ባለበት በአሁኑ ወቅት ሕዝብን ለተቃውሞ መጥራትና ከመስከረም 30 በኋላ መንግሥት የለም በማለት ብጥብጥ ለማንሳት የሚደረግ እንቅስቃሴ ተቀባይነት የለውም” ያሉት የክልሉ የኮሚኒኬሽን ጉዳይ ጽ/ቤት ሓላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ፤ “የመንግሥት ሥልጣንን ከምርጫ ውጪ በአቋራጭ ለመያዝ የሚደረገው ጥረት  ተቀባይነት እንደሌለው በድጋሚ ማስታወስ እንፈልጋለን” ብለዋል።
“እነዚህ ኃይሎች ስልጣን ለመያዝ ሲሉ ሰው ቢሞት ለእነሱ ምንም ማለት አይደለም። የሞት ጥሪ ለሕዝቡ እያደረጉ ነው፤ ይህ ትልቅ ስህተት እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል” ሲሉም በክልሉ የሚንቀሳቀሱት እንደ ኦፌኮ፣ ኦብፓና ኦነግ አይነቶቹ ፓርቲዎች ያላቸውን ድብቅ ዓላማ አጋልጠዋል።
ኮሮናቫይረስ በሽታ እየተስፋፋ ባለበት በአሁኑ ወቅት ሰዎችን ለተቃውሞ ሰልፍ ወደ አደባባይ መጥራት ተቀባይነት የሌለው ድርጊት እንደሆነ ያመላከቱት ሓላፊው ይህን እያስተባበሩ ያሉ ኃይሎች በአቋራጭ ሥልጣን ሲሉ ለመያዝ ከማሰብ ውጪ ለሕዝብ የሚፈይድ አንዳችም የረባ ነገር የላቸውም በማለት ገልጸዋቸዋል።
“መሳሪያ በመተኮስ፣ የመንግሥት ባለስልጣናትን በመግደል፣ በማስፈራራት እና የታችኛው የመንግሥት መዋቅርን በመናድ የሚገኝ ሥልጣን የለም” በማለት ኹከት ናፋቂ የሆኑት ጽንፈኛ ብሔርተኞችን ያሳሰቡት አቶ ጌታቸው ባልቻ ፤ “ለ27 ዓመታት ይህችን አገር ዘረፈው፤ ይህም አልበቃ ብሏቸው በመቀሌ መሽገው ተቀምጠው አገሪቷ ሰላም የሚነሱ ቡድኖችም፤ የክልሉን ሠላም ለማደፍረስ እየሠሩ” ነው በማለት ከሰዋል።
 “ኦሮሚያን የግጭት ሜዳ ለማድረግ፣ ኦሮሚያ ካልተረበሸች ኢትዮጵያን መረበሽ አንችልም የሚል ስልት ቀይሰው፤ በኦሮሚያም ግጭት እንዲፈጠር ድጋፍ የሚያርጉ እና የእነሱ ተላላኪዎች፣ ይህ አካሄድ የሚያዛልቃቸው ባለመሆኑ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ መንግሥት ጥሪ ያቀርብላቸዋል” ብለዋል።

LEAVE A REPLY