ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ከሰሞኑ በኢትዮጵያና በሱዳን ድንበር መሀል የተነሳውን ግጭት ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ምላሽ ሰጠ።
ግንቦት 20 ቀን 2012 ዓ.ም ኢትዮጵያና ሱዳንን በሚያዋስነው የድንበር አካባቢ በተፈጠረው ክስተት ማዘኑን የገለፀው የኢትዮጵያ መንግሥት፤ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ነው ዛሬ መግለጫ የሰጠው።
በተፈጠረው ግጭት በኢትዮጵያም ሆነ በሱዳን በኩል ጉዳት ለደረሰባቸው ጥልቅ ሐዘኑን ገልጾ፤ ይህ ክስተት በሁለቱ አገራት ሕዝቦች መካከል ያለው ጥብቅ ትስስር የማይወክል ነው ብሎታል።
በድንበር አካባቢ ያለውን ሁኔታ ለመቆጣጠርና ተጨማሪ ውጥረትን ለማስወገድ ሁለቱ አገራት በክስተቱ ዙሪያ ያሉ ጉዳዮችን በጋራ ምርመራ እንዲያደርጉ የጠየቀው መግለጫ፤ አሁን ላይ ሁለቱ አገራትን ወደ ግጭት የሚያስገባ ተቀባይነት ያለው ምክንያት ስለሌለ በድንበር አካባቢ ያሉ ክልላዊ አስተዳደሮች በመተባበር የሠላምና የደኅንነት ሁኔታውን ማረጋገጥ እንዳለባቸውም ጠቁሟል።
በድንበር አካባቢ የሚከሰቱ ችግሮች በሁለቱ አገራት መካከል ባለው ወዳጃዊ ግንኙነት መሰረት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፍትኄ ማግኘት እንደሚገባቸው የገለፀው የኢትዮጵያ መንግሥት፤ የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በካርቱም የሚገኘውን የኢትዮጵያ የኤምባሲ ተወካይን ጠርቶ ስለጉዳዩ ማብራሪያ በመጠየቅ ማነጋገሩንም አስታውቋል።