ኢትዮጵያ ነገ ዜና–  የኢድ አልፈጥር በዓል ከተከበረበት ቀን ጀምሮ ለተከታታይ ስድስት ቀናት ከተጾመ በኋላ፤ ከስድተኛው ቀን ምሽት ጀምሮ እስከ ማግስቱ 10 ሰዓት ድረስ የሚከበረው የ”ሸዋል ኢድ” በዓል በሐረር ተከበረ።

በተለይ የሐረሪ ብሔረሰብ ወጣቶች ትኩረት ሰጥተው የሚያከብሩት ይህ በዓል ቱሪስቶችና ሌላውም የኅብረተሰቡ ክፍል በዓል በሚዘጋጅበት ጀጎል ድረስ በመሄድ በአንድነት ሲያከብሩት ቢቆዮም ዘንድሮ ግን የኮሮና ቫይረስ መመሪያን ተከትሎ እንዲከበር ተደርጎል።
ወጣቶች የሚተጫጩበት መልካም አጋጣሚ ተደርጎ የሚቆጠረው የሸዋል ኢድ፤ በሐረሪ ክልል በሚገኘው የጨለንቆ ሰማዕታት አዳራሽ የተለያዩ አድባራት ዛኪሮች ተገኝተው፣ ርቀታቸውን በመጠበቅና ከንክኪ ነጻ በመሆን ውዳሴ ማድረጋቸው ታውቋል።
ለወትሮው በአደባባዮችና በመስጊድ የሚከበረው በዓል ላይ ከተገኙ ታዳሚዎች መካከል ሀጂ መሀመድ ሐሺም፤ በዓሉ የሐረሪዎችንና የሐረርን እሴት የሚሳይ በመሆኑ ሁሉ ጊዜ  በድምቀት አከብረዋለሁ፤ በዓሉ በሚያዘው መሰረት የተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሐረሪዎች በቫይረሱ ምክንያት ተጽዕኖ ለደረሰባቸው አቅመ ደካሞችን ይረዱበታል ። ጥላቻ ይወገዳል ። አንድነትና አብሮነት ይጎለብታል“ ሲሉ ተናግረዋል።
የክልሉ የባህል ፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ሓላፊ አቶ ዲኒር ረመዳን ፤ ” ሸዋል ኢድ በዓል የሐረሪ ብሔረሰብ ለበርካታ ዓመታት ሲያከብረው ኖሯል ። በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችና ቱሪስቶች ወደ ከተማዋ መጥተው የሚያከብሩት፣ አንድነታቸውን የሚያሳዮበት ትልቅ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ በዓል ነው” በማለት ቀኑንና ክብረ በዓሉን ገልፀውታል።

LEAVE A REPLY