ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡–“ደህና ቆዩ ” የሚል መጠሪያ የተሰጠው የኢትዮጵያ 5ኪ.ሜ ቨርቹዋል ሩጫ ዛሬ መጀመሩ ተነገረ።
ይህ ቨርቹዋል ሩጫ ለ 7 ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን፣ የውድድሩ የመጨረሻ ቀን እሁድ እለት ግንቦት 30 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚሆንም ከዝግጅት አስተባባሪዎቹ መግለጫ ሰምተናል።
500 ተሳታፊዎች የሚሮጡበት የቨርቹዋል ውድድር በስልክ ላይ በሚጫን የሩጫ መተግበሪያ በመታገዝ የሚደረግ መሆኑም ታውቋል።
በዚህ ውድድር ላይ ተሳታፊዎች የሚያደርጉትን የመወዳደሪያ ቁጥር በራሳቸው ንድፍ፣ በተጨማሪም ጊዜውን የሚገልጽ የራሳቸውን መልእክት እንዲያዘጋጁ እድል ፈጥሯል።
የውድድሩ ተሳታፊዎችም ይዘው የሚሮጡትን መልእክት ባለፉት ሳምንታት ለታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሲያጋሩ የቆዮ ሲሆን ፤ በብሩክ የሺጥላ “እኔ ስጠነቀቅ የምወዳቸው ይድናሉ” በሚለው መልእክት የተጀመረው ይህ ውድድር፤ የመረዋ ኳየር አባላት “ለተስፋ ጮክ ብለን እንዘምር” የሚል የጋራ መልዕክት ያዘለ ዝማሬ አሰምተዋል።
“ማስክ ማድረግ ከቬንትሌተር ይሻላል” ፣ “ቤት መሆን አይሲዩ ውስጥ ከመሆን ይሻላል፣” “መዳኃኒት ከመውሰድ ጥንቃቄ መውሰድ” ይሻላል የሚሉ መልዕክቶችም በሩጫው ላይ ተላልፈዋል።
ለቨርችዋሉ ውድድር የተመዘገቡ ተሳታፊዎች በስትራቫ (Strava) መተግበሪያ በተከፈተው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ – ቨርችዋል ሩጫ ክለብ አባል እንደሚሆኑ እና ክለቡን ከተቀላቀሉ በኋላ ያደረጉዋቸው ልምምዶች ተመዝግበው፤ በሮጡት ርቀት ልክ ደረጃ እየወጣላቸው ተሳታፊዎች እርስ በርስ እንዲፎካከሩና ራሳቸውን በተሻለ እንዲያዘጋጁ ይበረታታሉ መባሉን ከአዘጋጆቹ መግለጫ መረዳት ችለናል።
ዛሬ ሰኞ ግንብት 24 ቀን በተካሄደው የመጀመሪያ ቀን 39 ተሳታፊዎች ሩጫውን ማድረጋቸው ተነግሯል።