ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የወጣው መግለጫን ተከትሎ የማጣራት ሥራ መጀመራቸውን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ወይዘሮ አዳነች አበቤ ገለፁ።
“ሰብኣዊ መብት የምናከብረው እና የምናስከብረው ለማንም ብለን ሳይሆን ለሕዝባችን እና ለፍትህ ስንል ነው” ያሉት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጓ፤ “መግለጫውን የማጣራት ሥራችንን አጠናቀን ምላሽ ለመስጠት በሂደት እያለን መግለጫው በተለያዩ ሚዲያ ተሰራጭቷል፤ አሁንም ቢሆን ዘገባዉን ከይዘቱ፣ ከአካሄዱ፣ እንዲሁም የጉዳዩን እውነተኛነት እና ገለልተኛነት የማጣራት ሥራችንን በቶሎ ለማጠናቀቅ እየሠራን ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።
በዚህም የማጣራት ሥራ በሚገኘውም ውጤት፣ ሪፖርቱ እውነት በሆነበት ልክ፣ መወሰድ ያለበቸውን እርምጃዎች እንወስዳለን በማለት የመንግሥታቸውን ቁርጠኝነት የጠቆሙት አዳነች አበቤ፤ በአንጻሩ ሀሰት በሆነበት ወይም በተጋነነበት አኳያ ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል ጋራ በመወያየት ሪፖርቱ እንዲስተካከል ጥረት እንደሚያደርጉም አሰታውቀዋል።
ሪፖርቱን አስመልክተው የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች ከእውነት የራቀና ወገንተኝነት ያልጠበቀ ነው ሲሉ ምላሽ መስጠታቸው ይታወቃል።