ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ከደቡብ ሱዳን ወደ ኡጋንዳ የገቡ 50 ያህል የትልልቅ መኪና አሽከርካሪዎች ኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው የሀገሪቱ የጤና ሚኒስትሯ ጄን አሰንግ ገለፁ።
ከእነዚህ የተመረመሩና ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሹፌሮች መሀል፤ 10 የሚጠጉት ኤርትራውያን መሆናቸው የሚኒስትሩ መግለጫ ያሳያል።
ሚያዝያ 28 ቀን አንድ ከኬንያ በማላባ ድንበር ወደ ኡጋንዳ ሲገባ የተመረመረ ኤርትራዊ በቫይረሱ መያዙን ያስታወሰው የሚኒስትሯ መግለጫ፤ በተጨማሪ ግንቦት 6 ቀን በተመሳሳይ ከታንዛንያ የመጣ፣ በግንቦት 8 ከደቡብ ሱዳን በኢለጉ ድንበር ሲገቡ የነበሩ አራት ኤርትራውያንም በቫይረሱ መያዛቸውን ይፋ አድርጓል።
ሌሎች 3 ኤርትራውያን ግንቦት 12 እና ግንቦት 19 ደግሞ ሌላ አንድ ኤርትራዊ ሹፌር በቫይረሱ ተይዘው ኡጋንዳ ውስጥ ሲገኙ፤ በትናንትናው እለትም አንድ ሰው በተመሳሳይ ሁኔታ በዛው ሀገር በቫይረሱ ተይዞ መገኘቱ ተገልጿል።
ለ30 አመታት በሹፍርና የሰራውና ላለፉት ሰባት አመታት ከኬንያ ወደ ጁባና ኡጋንዳ ደረቅ ወደቦች ጭነት በማመላለስ የሠራው ኤርትራዊ፤ “ከዚህ በፊት ከሞምባሳ ወደ ጁባ አምስት ቀን ይፈጅብኝ ነበር። አሁን ግን ከጁባ ወደ ናይሮቢ ለመግባት እንኳ አንድ ወር ወስዶብኛል” ካለ በኋላ፤ “በዚህ ምክንያት፤ እኔ መቅደም አለብኝ” በሚል ግፊያ በሹፌሮች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች ለቫይረሱ መስፋፋት ዓይነተኛ ሚና ተጫውታዋል በማለት ግምቱን አስቀምጧል።