ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ለሁለት እንዲከፈል በተደረገው የጉራጌ ዞን እነሞር እና ኤነር ወረዳ ሕዝባዊ ግጭቶች መቀስቀሳቸው እየተነገረ ነው።
በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን የሚገኘው የእነሞር እና ኤነር ወረዳ ለሁለት እንዲከፈል የክልሉ መንግሥት ውሳኔ ካሳለፈ አንድ ዓመት ከስድስት ወር ቢሞላውም በስፍራው ያሉ ችግሮች ግን እስካሁን ድረስ በቅጡ መቋጫ መፍትኄ ሳያገኙ እንደቀረ ነው የሚነገረው።
በስፍራው የነበረውን አለመግባባት ተከትሎ በመንግሥታዊ ጣልቃ ገብነት እነሞር ወረዳ ለሁለት ቢከፈልም አሁንም ነዋሪዎች በተለይም ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ተከትሎ ችግር አለ ሲሉ ይደመጣሉ።
በተለይም በወረዳው የመገር አካባቢ ነዋሪዎች ከአዲሱ መዋቅር ጋር በተያያዘ ያላቸው ጥያቄ ባለመመለሱ የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች ተነፍገናል በማለት እያማረሩ ናቸው።
በሌላ በኩል ከአካባቢው ላይ ለመንግሥት መግባት ያለበትን ቀረጥ እየከፈሉ አይደለም ሲል የወረዳው መስተዳድር በነዋሪዎች ላይ የሰላ ትችት በመሰንዘር ላይ ነው ተብሏል።
ይህን ተከትሎ ጥያቄ አለን የሚሉ ነዋሪዎች ከመንግሥት አካላት ጋር የጀመሩት ውዝግብ ትናንትና ዛሬ ወደ ግጭት አምርቷል።
አካባቢው ወደ ብጥብጥና ግጭት ቀጠና እየተቀየረ መሆኑን በስፍራው የሚገኙ ምንጭቹን በመጥቀስ አዲስ ማለዳ ዛሬ ዘግቧል።