ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በነቀምቴ ከተማ ጥቃቱ የተፈጸመው ትናንት ረቡዕ ግንቦት 27 ቀን 2012 ዓ.ም ከረፋዱ አምስት ሰዓት ገደማ ላይ ሲሆን፣ በጥይት ከተመቱት የአንደኛው የከተማዋ ፖሊስ አባል ሕይወቱ ሲያልፍ ሌላኛው ደግሞ ሆስፒታል ገብቶ በጽኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ እንደሚገኝ የከተማዋ ጸጥታ እና አስተዳደር ጽ/ቤት አስታውቋል።
“በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሰዎችን በማስፈራራት ከዚያም ጥቃት በሚፈጽመው በዚህ ቡድን የከተማው ሁለት የፖሊስ አባላት በሽጉጥ ተመትዋል።” ያሉት የጸጥታ ሓላፊው ሚስጋኑ ወቅጋሪ፤ ጥቃት ፈጻሚው የአባ ቶርቤ አባላት እንደሆነ አረጋግጠናል ብለዋል።
ሳጅን ደበላ እና ሳጅን አዱኛ የተባሉት የከተማው የፖሊስ አባላት፤ ነቀምቴ ከተማ ቀበሌ 05 በእግር እየተጓዙ እያሉ በጥይት መመታታቸው ታውቋል።
አባ ቶርቤ ወይም ባለሳምንት የተባለው ቡድን የተለያዩ የፌስቡክ ገጾችን በመጠቀም ጥቃት እፈጽምባቸዋለሁ የሚላቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር በገጹ ላይ እንደሚያሰፍር፣ የሳጀን ደበላ ስምም ከዚህ በፊት በቡድኑ የፌስቡክ ገጽ ላይ መስፈሩን ተከትሎ፣ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ተነግሮት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሲደረግ ነበር ያሉት የከተማዋ የጸጥታ ኃላፊ፤ ጥቃቱ መቼ ይፈጸማል? የሚለው ማወቅ ስለማይቻል ሁኔታው አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ገልጸዋል።