ሹመት የተሰጣቸው ዘጠኙ ኢትዮጵያውያን አምባሳደሮች ሥልጠና እየተሰጣቸው ነው

ሹመት የተሰጣቸው ዘጠኙ ኢትዮጵያውያን አምባሳደሮች ሥልጠና እየተሰጣቸው ነው

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ኢትዮጵያን በተለያዩ አገራት እንዲወክሉ በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የካቲት 24 ቀን 2012 ዓ.ም የተሾሙት 9 አምባሳደሮች ዛሬ ሥልጠና መውሰድ ጀመሩ።

በዓለም ላይ በተከሰተው የኮቨድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ስልጠናውን በታቀደው ጊዜ ለማከናወን እንቅፋቶች መግጠማቸውን የተናገሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገዱ አንዳርጋቸው፤ ይህ ሥልጠና በውጭ አገራት የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የተሾሙ አምባሳደሮች አገሪቱ ከምታራምደው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በመነሳት ከወቅታዊ፣ አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ጋር በማዛመድ የአገሪቱን ተሰሚነት ማጉላት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መሠረታዊ ብሄራዊ ጥቅም ከሀገሪቱ ህልውና፣ ሉዓላዊነት፣ አንድነት፣ ደህንነት እና ክብር ማስጠበቅ እንዲሁም ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ እድገትን ከማረጋገጥ ጋር በእጀጉ የተቆራኘ ከመሆኑ አኳያ፤ ተሿሚ አምባሳደሮች ይህንን በውል መገንዘብ እና ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
አምባሳደሮቹ በሚወከሉበት አገር በሚደረጉ የሁለትዮሽ እና ባለብዙ መድረክ የዲፕሎማሲ ስራዎች ንቁ ተዋናይ በመሆን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት በትብብር መስራት፣ የውጭ ኢንቨስተሮችን የመሳብ፣ ለኢትዮጵያ የወጪ ምርቶች ገበያ ማፈላለግ፣ የኢትዮጵያን የቱሪዝም መስህብና ቱባ ባህሎችን የማስተዋወቅ፣ በውጭ አገር የሚኖሩ ዜጎችን መብትና ጥቅም በማስጠበቅ ተቀዳሚ ዓላማቸው እንደሆነም በሥልጠና ጅማሬው ላይ ተገልጿል።
ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ 4 ቀናት የሚሰጠው ሥልጠና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከጎረቤት አገሮች፣ ከአፍሪካ አህጉር፣ ከመካከለኛው ምስራቅ፣ ከኤዥያ ፓስፊክ፣ ከአውሮፓ፣ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ በውጭ አገር የሚገኙ ዜጎችን መብትና ለአገራቸው የሚኖራቸው ሚና፣ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ እና መሰል ርዕሶች ነጥቦች ላይ በዘርፉ በቂ ልምድ፣ ክህሎትና ተሞክሮ ያላቸው ባለሙያዎች አምባሳደሮቹን ያሰለጥናሉ ተብሏል።

LEAVE A REPLY