ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ዓለም ዐቀፉ የዜና አውታር ቢቢሲ ቀደም ሲል ያስተላለፈውን ፕሮግራም የተወሰነውን ድምጽ ቆራርጦ በመጠቀም፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ላይ የሀሰት ዜና የሰራው የትግራይ ቲቪ ተጋለጠ።
የትግራይ ቴሌቪዥን “የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር የምያንማሯ መሪ አንግ ሳን ሱ ኪ የገጠማቸው አይነት ተመሳሳይ እጣ ፈንታ ይኖራቸዋል፤ ሲል ቢቢሲ ዘገበ” በማለት ነበር የፈጠራ ዜና ያሰራጨው። ድምፁ ተቆራርጦ የተቀጠለ፣ ፕሮግራሙም ከረዥም ጊዜ በፊት የተሠራ፣ የቀረበው ዜናም ፍጹም ሐሰት ነው ሲል ቢቢሲ ይፋ አድርጓል።
“ትግራይ ቲቪ በቅርቡ በዘጋቢያችን ቃልኪዳን ይበልጣል የቀረበን የድምጽ ቅጂ ቆርጦ በማውጣት ለዚህ ዘገባው ተጠቅሞበታል” በማለት የህወሓትን ሸፍጥ ያጋለጠው ቢቢሲ፤ ይህን የመሰለ ዘገባ ፈጽሞ አልሰራሁም ሲልም የትግራይ ቲቪ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ላይ የሀሰት ዜና ማቅረቡን አስታውቋል።