ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በአማራ ክልል በራያ ቆቦ ወረዳ አመራሮች ላይ ባለፈው ሳምንት የግድያ ወንጀል ፈጽመው ተሰውረው የነበሩ ሁለት ተጠርጣሪዎች እጃቸውን መስጠታቸው ተሰማ።
የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ስዩም መስፍን እና የሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጽሕፈት ቤት ሓላፊ አቶ መንገሻ ሞላ ሕይወታቸው ያለፈው እሁድ ግንቦት 23/2012 ዓ.ም ሕግ ለማስከበር ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር ኢትዮጵያ ነገ በወቅቱ መዘገቡ አይዘነጋም።
በግድያ ወንጀሉ ሲፈለጉ የነበሩት ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ወንድማማቾች ሲሆኑ፣ ጥቃቱን ከፈጸሙ በኋላ ተሰውረው ቆይተው ትናንት ወልዲያ ማረሚያ ቤት በመሄድ እጃቸውን መስጠታቸው ተነግሯል።
የራያ ቆቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ስዩም መስፍን እና የሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጽህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት አቶ መንገሻ ሞላ ባለ ትዳርና ሁለቱም የአንድ ልጅ አባት ነበሩ ተብሏል።