ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ኖርዌይ ኦስሎ የሚገኘው የኖቤል ኮሚቴ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ማድረጉ ትክክለኛ እንደነበርና ውሳኔውን አሁንም እንደሚያምንበት ገለፀ።
አንዳንድ አካላት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሰጠውን የኖቤል የሰላም ሽልማት ለመሻር ዳግም እያጤነ ነው በማለት የሚያወሩት ነገር ሀሰት መሆኑን ዛሬ ያመላከተው ኮሚቴው፤ “የዶክተር ዐቢይን የሰላም አሸናፊነት በተመለከተ ማረጋገጫዬን እሰጣለሁ፤ በፊትም ሆነ አሁን ሽልማቱ ለእርሳቸው መስጠቴን ዳግም ለማጤን አላሰብኩም ፣ ወደፊትም ለማጤን ፍላጎት የለኝም” ሲል አቋሙን ይፋ አድርጓል።
እውነታው ያጋለጠው አዘጋጅ ኮሚቴው ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ ሽልማት ከተበረከተ በኋላ መሻርን ፈፅሞ እንደማይፈቅድም አረጋግጧል። የኖቤል ሽልማት መሰጠት ከተጀመረ ከአሮፓውያኑ 1901 ጀምሮም የአንድም ተሸላሚ ሽልማት አለመሻሩንም በማስረጃነት አቅርቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለሰላም እና ለዓለም ዐቀፍ ትብብር ላደረጉት ጥረት፣ በተለይም በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ለ20 ዓመታት የዘለቀው የድንበር የይገባኛል ውዝግብ በሰላም እንዲፈታ ተነሳሽነትን በመውሰዳቸው፤ የ2019 የኖቤል የሰላም ተሸላሚ መሆናቸው ይታወሳል።