ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ሁሉም የቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት ተቋማት ተግባራዊ የሚሆን የኤሌክትሮኒክ ትምህርት ሲስተም አገልግሎት ተጀመረ።
የኢ-ለርኒንግ ወይም የኤሌክትሮኒክ ትምህርት ሲስተም ተማሪዎች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ከትምህርት ተቋሙ ቢርቁም፤ የማመር ማስተማር ሂደቱ እንዳይስተጓጎል እና ተማሪዎች በየቤታቸው ሆነው የኤሌክትሮኒክ ትምህርት እንዲያገኙ አስተዋጽኦው የጎላ ነው ተብሎለታል።
አማራጭ ሲስተሙ በቴክኖሎጂው ከአንድ ወር በላይ ሙከራ ተደርጎበት ውጤታማነቱ ታይቷል። የትምህርት ዘርፎቹ በተግባር የተደገፈ መሆኑን ተከትሎ የትምህርት አሰጣጡ ይህን ያማከለ እንዲሆን መደረጉ ታውቋል።
የአዲስ አበባ ቴከኒክ እና ሞያ ትምህርትና ስልጠና ኤጄንሲ ከኤል ጂ ኮይካ ሆፕ ቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት እና ስልጠና ኮሌጅ ጋር በመተባበር ይፋ ያደረጉት ይህ ቴክኖሎጂ፤ ወረርሽኙ የሰዎችን እንቅስቃሴ የሚገድብ በመሆኑ ተማሪዎቹ በቤታቸው ሲቆዩ በቴክኒክ እና ሞያ ኮሌጅ የሚሰጠውን 30 በመቶ በንድፈ ሐሳብ፣ 70 በመቶውን ደግሞ በተግባር የተደገፈ ትህምርት እንዲያገኙ ለማስቻል ታቅዶ የተሠራ ነው ተብሎለታል።
አዲሱ የትምህርት አሰጣጡን ተግባራዊ ለማድረግ አንጋፋው የአቃቂ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተመርጦ ርክክብ መደረጉን ለማወቅ ተችሏል።
ትምህርቱ በኢንተርኔት አማካኝነት የሚሰጥ መሆኑን ተከትሎ መቆራረጥ እንዳይኖር ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ስምምነት የተደረገ ሲሆን፤ ሥልጠናው ለተማሪዎች በኮምፒዩተር አልያም በስማርት የእጅ ስልኮች እንደሚሰጥ ኤና ለዚህ አቅም የሌላቸው ተማሪዎች በእርዳታ የስልኩ ባለቤት እንዲሆኑ መደረጉ ተሰምቷል።