ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በሚያዚያ ወር ብቻ ከግብርና፣ ከማኑፋክቸሪንግ፣ ከማዕድን ምርቶች ዘርፍ እና ከሌሎች ምርቶች 329.3 ሚሊየን ዶላር ገቢ አግኝቻለሁ ሲል የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒሴቴር ገለፀ።
በወሩ 365.1 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተገኘው ውጤት 90 በመቶ ሆኖ እንዲመዘገብ አስችሎታል። ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ከተገኘው 249.5 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ጋር ሲነጻጸር የ32 በመቶ ብልጫ እንዳለውም ሚኒስቴር መ/ቤቱ አስታውቋል።
ኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዓለም ላይ ከፍተኛ ስጋት በሆነበት ወርሃ ሚያዚያ ከግብርናው ዘርፍ 237.47 ሚሊየን፣ ከማኑፋክቸሪንግ 23.18 ሚሊየን፣ ከማዕድን ዘርፍ 64.50 እና ከሌሎች ምርቶች 4.14 ሚሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቷ የሀገሪቱ ኢኮኖሚን የበለጠ እንዳይዳከም ያደርገዋል ተብልለታል።
ከተጠበቀው ዕቅድ በላይ ስኬታማነት ያሳዮት ዋና ዋና የወጪ ንግድ ምርቶች ወርቅ፣ አበባ እና ቡና ናቸው ያለው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒሴቴር፤ በአንጻሩ ቅመማ ቅመም፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ የቁም እንስሳት፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች እንደ ቅደም ተከተላቸው ከተያዘው ዕቅድ አኳያ ከ50 ከመቶ በታች ዝቅተኛ ውጤት ያስመዘገቡ መሆኑንም ገልጿል።