ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ጥቁር አሜሪካዊውን ጆርጅ ፍሎይድን እጁ ከኋላ እንደተጠፈረ ከመሬት ላይ አጣብቆ፣ አንገቱን በጉልበቱ ለዘጠኝ ደቂቃ የተጫነው ነጭ ፖሊስ የሰው ሕይወት በማጥፋት ወንጀል ፍርድ ቤት ቀረበ።
ነጩ ፖሊስ ፍርድ ቤቱ 1.25 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ዋስ እንዲያቀርብ በፍርድ ቤቱ ተጠይቋል።
ወንጀሉ ከፍተኛ ከመሆኑ አንፃር፣ እንዲሁም በበርካታ ግዛቶች የተነሳው ተቃውሞና ቁጣን ተከትሎም ተጠርጣሪው ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ የገንዘብ ዋስ እንዲያቀርብ መጠየቁን ዐቃቤ ሕግ ገልጿል።
ፖሊስ ዴሪክ ቾቪን በሁለተኛ ደረጃ ነፍስ ማጥፋት ወንጀል ክስ የሚቀርብበት ሲሆን፤ ድርጊቱን በዝምታ ሲመለከቱ የነበሩት ሦሥቱ ፖሊሶች ደግሞ በግድያ ወንጀል ተባባሪ በመሆን ይከሰሳሉ መባሉ ተሰምቷል።
በፈጸሙት ነውረኛ ድርጊት ምክንያት ዴሪክ ቾቪንን ጨምሮ ሦስቱ ፖሊሶች ከሥራ መባረራቸውን የጠቆመው ቢቢሲ፤ በፖሊስነት ለአስራ ዘጠኝ አመታት ያገለገለው ዴሪክ ቾቪን በትናንትናው ዕለት በኢንተርኔት አማካኝነት በተደረገ የፍርድ ሂደት ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት መቅረቡን አረጋግጧል።
ለ15 ደቂቃ ብቻ በዘለቀው የፍርድ ሂደት ላይ ግለሰቡ አንድም ቃል ያልተነፈሰ ሲሆን፤ እጁ በሰንሰለት ታስሮ፣ ብርቱካናማ የመለዮ ልብስ በማጥለቅ አነስተኛ ጠረጴዛ ትይዩ ተቀምጦ እንደነበርም እየተነገረ ነው።
ዴሪክ ቾቪን የጆርጅ ፍሎይድን ቤተሰቦች በምንም መንገድ እንዳያገኝ፣ የጦር መሳሪያውን እንዲያስረክብና የፍርድ ሂደቱም እስኪጠናቀቅ ከፀጥታ ኃይል አባልነቱ እንዲሰናበት የሚሉ ቅድመ ሁኔታዎችን ያስቀመጡት ዳኛዋ ጂኒስ ኤም፤ ተጠርጣሪው ውጭ ሆኖ ጉዳዮን መከታተል ከፈለገ፤ 1.25 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ዋስ እንዲያቀርብ አዝዘዋል።