ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኮሮና ወረርሽኝ ባስከተለው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ የተነሳ የአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪ በያዝነው ዓመት 2 ቢሊዮን ዶላር እንደሚከስር ተነገረ።
ጊዜው ለዘርፉ በታሪክ እጅግ መጥፎው አጋጣሚ ይሆናልም ሲል ዓለም ዐቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር ዛሬ ይፋዊ ሪፖርት አቅርቧል።
ከዚህ በመነሳት የአፍሪካ አየር መንገዶች ባለፈው ታኅሳስ ወር ከተገመተው 200 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ ባሻገር፣ በአጠቃላይ 2 ቢሊየን ዶላር ገቢ እንደሚያስገኙ የጠቆመው ሪፖርት፤ በዓለም ደረጃ የአየር ትራንስፖርቱ ዘርፍ 84 ቢሊዮን ዶላር ይከስራል በማለት ግምቱን አስቀምጧል።
በተጨማሪም በአፍሪካ ውስጥ በአየር ትራንስፖርቱ ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙ የሦስት ሚሊየን ሰዎች የሥራ ዕድልም ስጋት ላይ ወድቋል ሲል የችግሩን ጥልቀትም አስረድቷል።
አፍሪካ ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ አየር መንገዶች ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት ተጨማሪ አውሮፕላን ለመግዛት በሂደት ላይ የነበሩ ሲሆን፤ አሁን ግን ግዢዎችን የመሰረዝና የማዘግየት ውሳኔያቸውን እያስታወቁ ነው።
ኤርባስ የተሰኘው አውሮፕላን አምራች ኩባንያ አንዳንድ አየር መንገዶች አዘዋቸው በሂደት ላይ በነበሩ አውሮፕላኖች ምክንያት ክስ እንደሚመሰረት ሰኞ ዕለት ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም።
በአፍሪካ ውስጥ ከፍተኛ ብዛት ያለው አውሮፕላን ከኤር ባስ ያዘዘው አዲሱ የናይጄሪያ አየር መንገድ ግሪን አፍሪካ ኤር ሲሆን፣ ተቋሙ 50 ኤ 220 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ትዕዛዝ ሰጥቶ እንደነበር በመነገር ላይ ነው።
ሆኖም ወረርሽኙን ተከትሎ በተፈጠረ ችግር ምክንያት የገንዘብ እጥረት በመከሰቱ እየተንገዳገደ ያለው አየር መንገዱ፤ እንኳን አዲሶቹን አውሮፕላኖች ሊቀበል ይቅርና በሥራው ላይ ለመቆየት ሲል የተወሰነ ንብረቱን በመሸጥ ላይ መሆኑን መረጃዎች እየጠቆሙ ነው።