ከጥቂት ቀናት በኋላ በላሊበላ የሚከሰተውን የፀሐይ ግርዶሽ ለማየት መሞከር አደጋ አለው ተባለ

ከጥቂት ቀናት በኋላ በላሊበላ የሚከሰተውን የፀሐይ ግርዶሽ ለማየት መሞከር አደጋ አለው ተባለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በያዝነው ወር አጋማሽ በሀገራችን ይከሰታል ተብሎ የሚጠብቀው የፀሐይ ግርዶሽ ከዓመታት ቆይታ በኋላ የሚታይ በመሆኑ፣ ሰዎች ለማየት ካላቸው ጉጉት አንፃር በአይናቸው እና በተለያዩ ዘዴዎች ለመመልከት ሙከራ ካላደረጉ ለጉዳት ይዳረጋሉ ተባለ።

የፀሀይ ግርዶሹ የፊታችን ሰኔ 14 በኢትዮጵያ እንደሚከሰት የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መግለፁ አይዘነጋም።
ኢትዮጵያ በስነ ፈለክ ታሪክ ለዓለም የምርምር መረብ አሻራዋን አሳርፋለች ያሉት የስነ ከዋክብት ተመራማሪው ዶክተር ጌትነት ፈለቀ፤ በመጪው ሰኔ 14 በኢትዮጵያ የሚከሰተው ቀለበታማው የፀሀይ ግርዶሽ ይታይባቸዋል ተብሎ ከሚጠበቁ ሀገራት ኢትዮጵያ ካለው የአየር ጠባይ አንፃር ተመራጭ እንደሚያደርጋትም ገልፀዋል።
“በኢትዮጵያ በፃድቁ ዩሐንስ ዘመነ መንግሥት ንጉሥ ፍርድ ላይ እንዳሉ አንዳች ነገር ከሰማይ ተመለከቱ ፍርዳቸውም ወደ ምህረት ተለወጠ ” ሲሉ ምሳሌ ያቀረቡት ባለሙያው ፤ የስነ ፈለክ ክስተቶች ከተለመደው ክንውን ለየት ያለ በመሆኑ፣ ሰዎች ፍርኃት ስለሚያድርባቸውም ከእምነት ጋር ያያይዙታል ብለዋል።
የፀሀይ እና የጨረቃ ግርዶሽ በዓመት ውስጥ ቢያንስ 7 ጊዜ ሊከሰት እንደሚችል የስነ ፈለክ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። የፀሐይ ግርዶሽ ጨረቃ በፀሐይና መሬት መሀል ስትገባና ፀሐይን እንዳናያት ስትጋርድብን የሚፈጠር ክስተት ነው ተብሏል።
በቅርቡ ይሆናል የተባለው ክስተት ዓለም ዐቀፋዊ እንደሆነና ከማዕከላዊ አፍሪካ ኮንጎ ተነስቶ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ፣ ኦማን፣ የመን፣ ፓኪስታን፣ ታይዋን፣ ህንድ እና ቻይናን አቋርጦ ፓስፊክ ውቂያኖስ ላይ እንደሚያበቃም ታውቋል።
ክሴተቱ በላስታ ላሊበላ በጉልህ ሊታይ እንደሚችል የተናገሩት ዶክተር ጌትነት፤ ቀጣዩ ግርዶሽ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው ከ18 ዓመት በኋላ፣ በተጨማሪም ከ40 ዓመት በኋላ እንደሆነ አስረድተዋል።

LEAVE A REPLY