ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት ስለ ኤች አይ ቪ ኤድስ ይሰጥ የነበረው የግንዛቤ ማስጨበጫ እንቅስቃሴ መዳከሙን ተከትሎ በኢትዮጵያ በቫይረሱ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው ተባለ።
በኢትዮጵያ ከ100 ሺኀ በላይ ሰዎች በኤች አይ ቪ ኤድስ ተይዘው፣ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ መኖሩን ሳያውቁ እንደሚኖሩም የፌዴራል ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ጽሕፈት ቤት ይፋ አድርጓል።
በተለይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የታየው መዘናጋት በቫይረሱ የሚጠቁ ሰዎችን ቁጥር እንዳሳደገው የገለጸው ጽ/ቤቱ ፤ በኢትዮጵያ ከ669 ሺኅ በላይ ሰዎች በኤች አይ ቪ ቫይረስ እንደተያዙም አስታውቋል።
የፌዴራል ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ ዳንኤል በትረ እንደሚሉት ከሆነ በአሁኑ ወቅት ኤች አይ ቪ በደማቸው እንዳለ ተመርምረው ራሳቸውን በማወቅ መድኃኒት እየወሰዱ ያሉት 483 ሺኅው ብቻ ናቸው። ቀሪዎቹ 186 ሺኅ ሰዎች በምርመራ እራሳቸውን ሳያውቁ እየኖሩ ናቸው ብለዋል ሓላፊው።
አሁን ላይ በኤች አይ ቪ ከሚጠቁ ሰዎች ከ15 ዓመት እሰከ 24 ዓመት የዕድሜ ክልል የሚገኙት ታዳጊዎች አብዛኛውን ቁጥር መያዛቸው የችግሩን አስከፊነት እንደጨመረው የገለፁት አመራሩ በዚህ ወቅት በሀገሪቱ በተስፋፋው የኮሮና ቫይረስ የኤች አይ ቪ ታማሚዎች ከተጠቁ የመትረፍ እድላቸው አነስተኛ በመሆኑ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ መክረዋል።
በኢትዮጵያ አሁን ላይ ባለው ትክክለኛ መረጃ መሠረት በቀን 31 ሰዎች፣ በዓመት 12 ሺኅ ሰዎች በኤች አይ ቪ ኤድስ የሚምቱ ሲሆን፣ በቀን 61፣ በዓመት 23 ሺኅ ሰዎች አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ሆነው እንደሚመዘገቡም ከዶክተር ዳንኤል በትረ መግለጫ መረዳት ችለናል።