ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኢትዮጵያ ሕዝብ በሀገሩ ሕልውናና ክብር ከመጡበት ሞት የማይፈራ ጀግና ሕዝብ መሆኑን እንኳን ግብፅ ማንም ያውቀዋል ሲሉ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።
የግብፅ መሪዎች የተሳሳተ አስተሳሰብ ሀገሪቱን በከፍተኛ ደረጃ ይጎዳታል ያሉት ጀነራል ብርሃኑ ጁላ፤ ” ግብጾች ኢትዮጵያዊያን ጦርነት ከመጣ እንዴት ጦርነትን መሥራት እንደሚችሉ በሚገባ ያውቁታል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በሀገሩ ሕልውናና ክብር ከመጡበት ሞት የማይፈራ ጀግና ሕዝብ መሆኑን አይደለችም ግብጽ ዓለም ያውቃል። የጦር መሣሪያ በገፍ መሰብሰብ ብቻ በጦርነት ውስጥ ለድል አያበቃም” በማለት ተናግረዋል።
በጦርነት ውስጥ ለድል የሚያበቁ ሳይንሳዊ የሆኑ የጦርነት መሰረታዊ የሚባሉ ሕጎች እንዳሉ አሉ የሚሉት ም/ ኢታማዦር ሹሙ፤ “እነዚህ ለድል የሚያበቁት የመሰረታውያኑ ቁልፎች በሙሉ በኢትዮጵያውያን እጅ ናቸው፤ ግብጾች 30 እና 40 ዓመት ሙሉ የሰበሰቡት ብዙ ዓይነት የጦር መሣሪያ አላቸው፤ በዚህ አስፈራርተው የጋራ የሆነውን ውሃ እንዳትነኩ ለማለት ይሞክራሉ። መሪዎቿ በዚህ መልኩ ማሰብ አልነበረባቸውም። ግብጻዊያን ከኢትዮጵያ ጋር በጭራሽ መጣላት ሳይሆን ኢትዮጵያንን ተንከባክበው በመያዝ ውሃውን እንዴት አድርገን በጋራ እንጠቀም ማለት ነበረባቸው” ሲሉም ተደምጠዋል።
” ፈጣሪ ውሃውን ኢትዮጵያ ውስጥ ፈጠረው፤ ወደ ሱዳንና ግብጽ እንዲፈስ አደረገው፤ የወንዙ ውሃ ኢትዮጵያ፤ ሱዳን፤ ግብጽም ላይ ጥቅም ላይ ይውላል” በማለት አባይ የተፈሰስ ሀገራቱ፣ በተለይም የሦስቱ ሀገራት የጋራ ጥቅም መሆኑን ያመላከቱት ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ከዚህ ውጭ ልማታችንን ወደ ኋላ የሚጎትት ማንኛውንም እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ አትቀበልም ሲሉ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ ላይ ገልጸዋል።
ከዚህ ባለፈ ከላይ ያለው ሀገር እንጂ ከታች ያለው ሀገር ውሃውን መጠቀም አይችልም የሚለው እሳቤ አያስኬድም፣ የዓለም ሕግም አይደግፈውም፤ ይሄ የተሳሳተ የመሪዎቿ አስተሳሰብ ግብጽን በከፍተኛ ደረጃ ይጎዳታል ብለዋል ።“ግብጽ አሁን የያዘችው መንገድ ለሀገሪቱ ብዙ ጠላት የሚያፈራባት ነው፤ ጠላትነት በጨመረ ቁጥር ጭራሹንም ውሃው ሙሉ በሙሉ የእኔ ነው ወደሚል የእልህ መንገድ ይወስዳል” ያሉት ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹሙ፣ መቼም ቢሆን የግብጽ ሠራዊት ኢትዮጵያ ገብቶ ምሽግ ሠርቶ የዓባይን ገባር ወንዞች አይጠብቅም፤ የኢትዮጵያን ምድርንም አይረግጥም፤ እነዚህ ወንዞቻችን ከጦርነትም በላይ ታላቅ አቅምና ጉልበት አላቸው ብለዋል።