ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በኢትዮጵያ ለ2013 በጀት ዓመት የጸደቀውን በጀት ተከትሎ ለክልሎች የተከፋፈለው ዓመታዊ በጀት ሲዳማ ክልልን አለማካተቱ ከምክር ቤት አባላት ዘንድ ተቃውሞ ተሰምቶበታል።
ዛሬ የገንዘብ ሚኒስትሩ የ2013 ዓ.ም የበጀት ድልድልን ይፋ ሲያደርጉ በቅርቡ አስረ አንደኛ ክልል በመሆን ሕጋዊ መስፈርትን ያሟላችው ሲዳማም በበጀቱ ውስጥ እንደ አንድ ክልል በጀቱ በተናጠል ይደርሳታል ተጠብቆ ነበር።
ይሁንና የቀጣይ ዓመቱ በጀት እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ለዐሥሩ ክልልች ብቻ የተመደበ መሆኑን የሚያሳየው የገንዘብ ሚኒስቴሩ ሪፖርት መቅረቡን ተከትሎ በምክር ቤት አባላት ዘንድ ተቃውሞ ቀርቧል።
በተለይም አቶ ጴጥሮስ የተባሉ የምክር ቤት አባል (የሲዳማ ተወላጅ የሆኑ) ሲዳማ ክልል መሆኗ ከተረጋገጠ በኋላ እንዴት በበጀት ውስጥ ሳትካተት ቀረች? የሚል ጥያቄ አቅርበዋል።
መንግሥታዊ በጀት የሚመደበው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የክልል ቀመር ድልድል መሠረት መሆኑን የጠቆሙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሺዴ፤ በዚህ አሠራር መሠረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሲዳማን በክልሎች በጀት ድልድሉ ውስጥ አካትቶ ባለመላኩ ፣ በመጣው መስፈርት መሠረት ድልድሉ እንደተካሄደ እና ወደ ፊት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የክልል ድልድል ቀመሩ ውስጥ ሲዳማን አካቶ ከላከ ማስተካከያ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።