ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– “የትግራይ ክልል ምክር ቤት ምርጫ ይካሄድ ብሎ መወሰኑ ህገ መንግሥቱን የሚጻረር ስለሆነ መንግሥት የምርጫ ቦርድን ውሳኔ አክብሮ ያስፈጽማል” ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሓላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን አስታወቁ፡
ምርጫን የማስፈፀም ሥልጣን የተሰጠው ምርጫ ቦርድ ስለሆነ ሌላ አካል በዚህ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ልግባ ካለ፣ ከሥልጣን ገደቡ በላይ የምርጫ ቦርድን ሥልጣን መጋፋት እና መዳፈር ስለሆነ መንግሥት የምርጫ ቦርድን ውሳኔ አክብሮ ይፈጽማል ሲሉ አቶ ንጉሡ ተናግረዋል።
“መከላከያ ሠራዊቱ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ የሀገርን ሉዋላዊነትና ህገ መንግሥቱን እንደሚያስከብር ሁሉ ምርጫ ቦርድም የተሰጠውን ህገ መንግሥታዊ ሥልጣን ሁሉም አካል ሊያከብር ይገባል” ያሉት የጽ/ቤት ሓላፊው፤ “አስፈፃሚ አካሉ በምርጫ ቦርድ ሥራ እና ውሳኔ ጣልቃ በመግባት ቢፈትፍት ያለ ሓላፊነቱ መንቀሳቀስ ስለሆነ መንግሥት የምርጫ ቦርድን ውሳኔ ያከብራል፣ ይፈፅማል” ብለዋል።
“በኢትዮጵያ ታሪክ ምርጫ ቦርድ የተሻለ እና ገለልተኛ ሆኖ እንዲቋቋምና ለእውነተኛ ዴሞክራሲ መጎልበት በር አድንዲከፍት ሆኖ ተደራጅቷል፤ የክልልም ሆነ የፌዴራል መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ልግባ ቢል ከሥልጣን ገደቡ በላይ የምርጫ ቦርድን ሥልጣን መጋፋት እና መዳፈር ይሆናል” ሲሉ የተናገሩት አቶ ንጉሡ ጥላሁን፤ የኢትዮጵያ መንግስት በአሁኑ ወቅት ዋነኛ ትኩረቱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በመከላከል የህዝብን ደህንነት መጠበቅ፣ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ የሚገጥመን የማደነቃቀፍ ፈተና በማለፍ ውሀ መሙላት መጀመር እና ለጥቅም ማብቃት መሆኑንም ገልጸዋል።