ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኮሮና በሽታ በተስፋፋበት በዚህ ወቅት በየመንደሩ የሚታረዱ የከብት ስጋዎችን ለኅብረተሰቡ የሚያቀርቡ ሉካንዳ ቤቶች ላይ እርምጃ መወሰዱ ተነገረ።
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ እንደ ገለፀው ከሆነ፤ በህገ ወጥ መንገድ የታረደ የ50 ከብት ስጋ እና ከ360 በላይ የበግ እና የፍየል ስጋ በቁጥጥር ሥር መዋሉን እና በ132 ልኳንዳ ቤቶች ላይ እርምጃ ተወስዷል።
የደንብ ማስከበር ዘርፍ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር፤ በዐሥሩም ክፍለ ከተሞች ከሌሊቱ 10፡00 ሰዐት ጀምሮ በተደረገ ድንገተኛ የኦፕሬሽን ሥራ ጨለማን ተገን አድርገው በህገ ወጥ መንገድ የበግ፣ የፍየል እና የበሬ እርድ ሲያከናውኑ በተገኙ ልኳንዳ ቤቶች ላይ እርምጃ ተወስዷል መወሰዱን የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሓላፊ ኮሚሽነር አዱኛ ደበላ ገልፀዋል።
በድንገተኛ የኦፕሬሽን ሥራ በህገ ወጥ መንገድ ከአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ውጪ የታረዱ የ50 የከብት ስጋ እና 360 የበግ እና የፍየል ስጋ በቁጥጥር ሥር እንደዋለ የሚያስረዳው ዜና፤ ለኮሮና ቫይረስን በይበልጥ በሚያስፋፋ እና ንጽህናውን ያልጠበቀ፣ እንዲሁም በሚመለከተው አካል ያልተመረመረ ስጋ ሲሸጡ በተገኙ 132 ልኳንዳ ቤቶች ላይ እርምጃ ተወስዷል ብሏል።
አብዛኞቹ ስጋ ቤቶች አንድ በሬ በቄራዎች ድርጅት እርድ ካከናወኑ ወይም ካዘዙ በኋላ ይህንን አሠራር ሽፋን በማድረግ፤ ተጨማሪ በሬዎችን ከቄራዎች ድርጅት እንደታረዱ በማስመሰል ህገ ወጥ ስጋ ለህብረተሰቡ በመሸጥ ላይ እንደሆኑ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን መ/ቤቱ ገልጿል።
ቀደም ባሉት ጊዜያትም እንዲህ ዓይነቱ የሉካንዳ ቤቶች ህገ ወጥ አሠራር የነበረ ቢሆንም አሁን የኮሮና ወረርሽኝ አስጊ በሆነበት ወቅት ጥራቱን ያልጠበቀ ስጋ ማቅረብ አደገኛነቱ የከፋ በመሆኑ፤ በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩ በርካታ ግለሰቦች እና የልኳንዳ ቤት ባለንብረቶች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ ነው ተብሏል።
ከፍተኛ እርድ በሚካሄድባት አዲስ አበባ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት፣ 90 በመቶ የከብት እርድ ፣ከ20 እስከ 30 በመቶ የበግ እና የፍየል እርዶች ከቄራዎች ውጪ በህገወጥ መንገድ በጫካ እና በወንዞች ዳርቻ እርድ እንደሚፈጸም ታውቋል።