ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ለተጨቆኑት የዓለም ሕዝቦች ሁሉ ቆሚያለሁ የሚለው አልቃኢዳ ሰሞኑን ባሰራጨው መልዕክት ሙስሊም አሜሪካዊያንን ብቻ ሳይሆን ሙስሊም ያልሆኑትንም በተቃውሟቸው እንዲገፉበት አበረታቷል።
“ኡማህ” የተሰኘው የአል ቃኢዳ የበይነ መረብ መጽሔት በሰሞነኛ ልዩ ዕትሙ፤ የጆርጅ ፍሎይድን ምስል ከፊት ለፊት አውጥቶ ከማተሙ ባሻገር መጽሔቱ የተጠቀመው ምስል የፍሎይድን የመጨረሻ የጭንቅ ሽርፍራፊ ሰከንዶችን የሚያሳይ ነው።
የአል ቃኢዳ ልሳን የሆነው ‘ኡማህ’ መጽሔት በእንግሊዝኛ መታተሙ በራሱ ድርጅቱ መልዕክቱ እንዲደርስለት የፈለገው ለአሜሪካዊያን እንደሆነ ያሳያል ያለው ቢቢሲ፤ አል ቃኢዳ “የአሜሪካ መውደቂያ መቃረቡ አይቀሬ” መሆኑን የተነተነበት፣ ከሁሉ በፊት ግን የአሜሪካ ምጣኔ ሀብት እንደሚንኮታኮት ቅድመ ግምቱን ያስመጠባቸው ጽሑፎች መካተታቸውን ዘግቧል።
“የትጥቅ ትግል በአሜሪካ ተቀጣጥሏል፤ የእርስ በርስ ጦርነት ደግሞ አይቀሬ ነው። ከዚህ ውጥንቅጥ የሚያወጣችሁ ታዲያ ዲሞክራቶች እንዳይመስሏችሁ፤ ከዚህ ቸግር የሚያወጣችሁ አል ቃኢዳ ብቻ ነው” ሲል በሽብርተኝነት የተፈረጀው አል ቃኢዳ ራሱን የአሜሪካ ነፃ አውጪ አድርጎ አቅርቧል።
አል ቃኢዳ ባለፉት ዓመታት በአይ ኤስ ተጋርዷል የሚለውን የበርካታ ተንታኞች ሐሳብ ያጣጣሉት በለንደኑ ኪንግስ ኮሌጅ የጽንፈኝነት ጥናት ዳይሬክተር ዶክተር ሺራዝ ማሄር፤ “አል ቃኢዳ አሁንም ቢሆን ከጀርባ ሆኖ ሥራውን እየሠራ ነው። በዓለም ዐቀፍ ጉዳዮች ላይ አሁንም ተሰሚነት ለማግኘትና ወደ መድረኩ ለመመለስ ፍላጎት አለው” ሲሉ ተናግረዋል።