ከመስከረም 30 በኋላ መንግሥት የለም ለሚሉ ኃይሎች መከላከያ ሠራዊቱ ዝግጁ መሆኑ ተነገረ

ከመስከረም 30 በኋላ መንግሥት የለም ለሚሉ ኃይሎች መከላከያ ሠራዊቱ ዝግጁ መሆኑ ተነገረ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና መጪው ከመስከረም 30/2013 ዓ.ም  በኋላ መንግሥት የለም የሚለውን ዛቻና ፉከራ ፣ ሕግና ሥርዓት የመጣስ እንቅስቃሴን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዳር ቆሞ አይመለከትም ሲሉ ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ገለፁ።

የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጀነራል ብርሀኑ ጁላ እንኳን መስከረም 30 የወደፊቶቹ መስከረሞች በሰላምና በተረጋጋ ሁኔታ ያልፋሉ ሲሉ ለኹከት ናፋቂዎች  ኮስተር ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል።
“ኢትዮጵያ ከምርጫ ታሪክ በፊት ነበረች፣ ዛሬም አለች፣ ወደፊትም ትኖራለች፣ ትቀጥላለችም። ከመስከረም በኋላ ሕግና መንግሥት የለም፣ ሀገሪቷ የትርምስ አረንቋ ውስጥ ትገባለች! ብሎ ማወጅ ኢትዮጵያ ሀገሬ ነች ከሚሉ ዜጎች አይጠበቅም” ያሉት ም/ ኢታማዦር ሹሙ እንዲህ ዓይነት ይሄ ትክክል ያልሆነና በሕግ ያስጠይቃል ብለዋል።
ሕገ መንግሥቱ ሥልጣን የሚያዝበትን መንገድ በግልጽ በማስቀመጡ፣ ሥልጣን ላይ ያለውም ኃይል ይህንን የሚያከብር  ነው ያሉት ጀነራሉ፤ “ከዚህ ውጪ በሰላማዊ የፖለቲካ ውድድር ውስጥ አልፈን ሥልጣን ማግኘት አንችልም ብለው ራሳቸውን ያሳመኑ ክፍሎች ሀገር ትጥፋ፣ ሕግ፣ ሥርዓትና መንግሥት የለም፣ አይኖርም! ቢሉ ተገቢነት የለውም” ሲሉ አሳስበዋል።
” መከላከያ ሠራዊት፤ የሕገ መንግሥቱን የበላይነት ጠባቂ ነው፡፡ መከላከያ ሁሉም ነገር በሕገ መንግሥቱ በተደነገገው መሠረት ብቻ እንዲተገበር የመጠበቅና የማስከበር ግዴታ አለበት፡፡ መንግሥት ወረርሽኙ እስኪገታ ምርጫ ያራዘመው የመንግሥት ሥልጣን ክፍተት እንዳይፈጠር፣ ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት የተሰጠ ሕገ መንግሥታዊ መፍትኄ ነው፡፡ ይሄ እርምጃ ሕገ መንግሥታዊ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ሠራዊታችን ሕገ መንግሥታዊ ሠራዊት ነው የምንለውም ለዚህ ነው” ሲሉ የሠራዊቱን ድርሻ ያብራሩት ጀነራል ብርሃኑ ጁላ  ለሕግ የበላይነት ሲባል መከላከያ ሠራዊቱ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ አረጋግጠዋል።

LEAVE A REPLY