የኢትዮጵያ ችግር የመሪዎቿ ቅድስና ማነስ ነው ብዬ አላምንም። መሪዎችም ሰዎች ናቸው። የመንግስት ሰራተኞችም ሰዎች ናቸው። ባለስልጣናትም ሰዎች ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሰው ነው። ዳኛውም ሰው ነው።
ችግራችን ከመሪዎች የቅድስና ጉድለት ይሻገራል።
ኢህአዴግ በብልፅግና ተተካ። አንዳንድ መሪዎችም ተቀየሩ።
የድሮው መሪዎች የሰሩት ግፍ በዶክመንተሪ፥ በመግለጫ፥ በክስ ተሰማ። ጉድ ጉድ አልን። እንደ የሰይጣን ልጆች ቆጠርናቸው። እነርሱን በቅዱሶች በመተካት መልካሙን ጊዜ ተመኘን። የቃልኪዳን ሀገርና ህዝብ አሁን ገና ከቃልኪዳኑ ጋር ተገናኘ ብለን አመንን።
ተስፋ ሰነቅን። እኔም አብሬ ሰነቅሁ። እጣፋንታችንን ያስተካክልልናል ብዬ የማምንባቸውን ስራዎች፤ አንዳንዶቹን መንግስትን በማገዝ፥ ሌሎቹን ደሞ ከሌሎች አካላት ጋር በመሆኑ የበኩሌን ለማድረግ ሞከርኩ።
እያደር ግን የተገነዘብኩት የብዙዎቻችን ተስፋ ሰዎች ላይ የተንጠለጠለ መሆኑን ነው። ቅዱስ ነው ያልነውን ሰው በመደገፍና ሰይጣን ያልነውን በማውገዝ። በዚህ የሚታየኝ አዙሪት ነው።
የህገመንግስት ትርጉም ጉዳይ ሲነሳም አስተያየቴን ከመፃፍና ከማጋራት አልፌ ሁለት ድርጅቶችን በማገዝ በሂደቱ እንደ አንድ ወገን ክርክራችን እንዲሰማ በይፋ አመለከትን። መልስ ሳናገኝ አጣሪ ጉባኤው አስተያየቱን ሰጥቶ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ፀደቀ። ምክር ቤቱ ከተጠየቀው በላይ ሄዶ ያልተጠየቀውንና መንግስትም ያስፈልገዋል ብሎ ያሰበውንም ጭምር ፈቀደለት።
አንድ ወዳጄ “ምን ነክቶህ ነው? ምን አይነት ውጤት አገኛለሁ ብላቹ ነው? በዚህ ቀውጢ ጊዜ አብይን በማገዝ ፈንታ በተቃራኒ ጎራዎች የቆምከው? አንተስ ብትሆን ምን አይነት ጥቅም አገኛለሁ ብለህ ነው?” ሲል ጠየቀኝ። እውነቱን ነው። ከቅንነት እንደሚመነጭ አልጠራጠርም።
የአብይ ሃሳቦችን፤ በአብዛኛው እደግፋቸዋለሁ። እርሱን መደገፍ ማለት ግን እንዳሻህ ሁን ማለት አይደለም። ሲጀመር ችግራችን ቅዱሱን መሪ ከማጣት ስለማይመነጩ።
እስከ ሞት ድረስ የታመኑ፤ በአደባባይ ለመስዋእት የሚወዳደሩ፤ ታጋዮች በጊዜ ሂደት ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ አይቻለሁና። ገና ከጧቱ በስኳር ከተታለሉት ጀምሮ ለመኖር የጓጉና በአደባባይ በማስመሰል ሲወዳደሩ አይቻለሁና።
የአዲስ አበባ መስተዳድር የጎዳና ላይ ልመናን እና ልገሳን በህግ ሊከለክል ነው የተባለ ሰሞን ስለ በጎነት ግብርና የፃፍኩትን ዳግም እንደሚከተለው ለጥፌዋለሁ።
**
*****የበጎነት ግብርና!*****
የሰው ልጅ ማለት፤ በደረቱ የበጎነትና የክፉነት ዘሮችን ይዞ የሚዞር ፍጡር ነው። ጭራሽ ጭራቅ የመሆን እድል አለው። ፍፁም መናንና ራስአልባ የመሆንም እድል አለው። እንዲሁም በእነዚህ መካከል።
በማንኛውም ሰአትና ቦታ፤ በባህሪያችን የሚገለጠው የበጎነትና የክፉነት ስብጥሩ የሚወሰነው፤ በሁላችንም ደረት ላይ ያሉትን እነዚህን የበጎነትና የክፉነት ዘሮች በሰጠናቸው የውሃ፥ የፀሃይ ብርሃን፥ የማዳበሪያ፥ የፀረአረም፤ መጠንና አይነት ነው።
**
ማን ነው ለእነዚህ ዘሮች ውሃ የሚያጠጣው? ፀሃይ የሚያወጣው? ማዳበሪያ፥ ፀረአረም የሚሰጠው? ማን ነው የሚያርመው፥ የሚጎለጉለው?
መዋቅሮች ናቸው። መዋቅሮች ማለት የሆነውን እንድንሆን የሚያደርጉን ነገሮች ናቸው። በዚህ ውስጥ ብዙ ነገር ይካተታሉ። ተቋሞት (ህግ፥ ባህል፥ እሴት)፥ እምነት (እና እውቀትና ልምምድ (ስሜት፥ ፍላጎት)፥ ምህዳር (ዲዛይን)፥ እና የመሳሰሉት።
**
በተለያየ አጋጣሚ ሁላችንም በተወሰነ መጠን ለጋስ እንሆናለን። ከራሳችን ጊዜ፥ ገንዘብ፥ እውቀት ቀንሰን ለሌላ እንሰጣለን። ምን ያህል? በምን ሁኔታ? የሚለው ከዚህ በላይ እንዳልኩት በመዋቅሮች ይወሰናል።
***
አንድ ሰው ታሞ፥ ተመርቆ፥ ወይም አግብቶ፤ የመዋጮ ወረቀት ቀርቦልህ ያውቃል?
የለጋሶች ስም ዝርዝርና የሰጡት የገንዘብ መጠን የተፃፈበት ወረቅት። አንተም ስምህንና ምን ያህል ለመስጠት ፈቃደኛ እንደሆንህ እንድትፅፍ።
ምን ያህል ታዋጣለህ? የምታዋጣው ገንዘብ ከአንተ ቀድመው በወረቀቱ ስማቸው የሰፈረው ሰዎች ባዋጡት ገንዘብ ይወሰናል?
“እረ በፍፁም” ልትል ትችላለህ። “ሰው እንደቤቱ እንጂ እንደጎረቤቱ አይኖርም” ልትል ትችላለህ። ግን አንደዛ ነው።
ጥናቶች የሚያሳዩት ሌላ ነው። የምታዋጣው ገንዘብ መጠን ሌሎች ባዋጡት ገንዘብ እንደሚወሰን ነው ጥናቶች ያሳያሉ።
***
አውቶብስ ውስጥ ነህ እንበል። አንድ የኔ ቢጤ ቀርቦ፤ መለመን ጀመረ።
አጠገብህ ያሉ ሰዎች ኪሳቸውን እየበረበሩ መስጠት ጀመሩ እንበል። አሁንስ ትሰጣለህ?
ማንም አልሰጠም እንበል። ይልቅስ አንዱ ተሳፋሪ ተነስቶ “አንተ አጭበርባሪ ባለፈው አስር አመት መርካቶ እንዲሁ ሚስቴ ታማብኝ እያልህ ስትለምን ነበር። የሆስፒታል በሽተኞችን እየመረጥክ ነው እንዴ ስታገባ የምትኖረው። አጭበርባሪ” ብሎ ጮኸ። አሁንስ ትሰጣለህ?
***
በአንድ መንደር ያሉ ሁለት የተለያዩ መንገዶችን አስብ። በአንዱ መንገድ የመንደሩ ነዋሪዎች የሚተላለፉት በነጠላና በተለያየ ጊዜ ነው እንበል። በሌላኛው መንገድ የመንደሩ ነዋሪዎች የሚተላለፉት በተወሰኑ ሰአታትና በብዛት ነው እንበል። በሁለቱም መንገዶች ሁለት የኔቢጤዎች ቁጭ ብለው ይለምናሉ። የትኛው ብዙ ገንዘብ የሚያገኝ ይመስልሃል?
በጎነትህን ሌሎች ሰዎች (በተለይ ደግሞ ተደጋጋሚ መስተጋብር ከእነዚህ ሰዎች ጋር ካለህ) በሚያዩበት ጊዜ፤ የበለጠ በጎ እንሆናለን። ማንም በጎነታችንን የማያይ ከሆነ ግን፤ የበለጠ ንፉግ እንሆናለን።
***
በጎነታችንን እና የበጎነታችንን መጠንና ሁኔታ በከባቢው በሚሰሙ ድምፆችና የመሳሰሉ ነገሮችም ሊወሰን ይችላል። ለዚህ ነው እንዴ የኔቢጤዎች ቤተሃይማኖት አካባቢ የሚበዙት?
አንድ ጥናት ላይ ሰዎች በሁለት ተከፍለው፤ በአንደኛው ቡድን ያሉት፤ ብዙ ፎቶዎች እንዲመለከቱ ተደረገ። ከፎቶዎቹ መካከል የተከመረ ዶላር ነበር። ሌላኛው ቡድንም ፎቶዎችን ተመልክቷል። ነገር ግን የዶላር ክምር አላዩም።
የትኞቹ ተበለጠ ቸር የሚሆኑ ይመስልሃል? የትኞቹ ንፉግ የሚሆኑ ይመስልሃል?
የዶላር ክምር ፎቶ የተመለከቱት የበለጠ ንፉግ እንደሚሆኑ ጥናቱ ያሳያል።
***
ሌላ ጥናት ላይ ደግሞ ሰዎች ቀላል ጥያቄዎችን በመመለስ ውድድር እንዲሳተፉ ተደረገ። በመመለሷቸው ጥያቄዎች ልክ የገንዘብ ሽልማት ያገኛሉ። ተሳታፊዎቹ ያላወቁት ነገር፤ የመለሷቸውና ያልመለሷቸው ጥያቄዎች በእነርሱ እውቀት አይወሰንም። ተመራማሪዎቹ ሆን ብለው፤ የተወሰኑት ተሳታፊዎች የሚሰጧቸው መልሶች ትክክል እንደሆነ ነግረዋቸው ብዙ ገንዘብ በሽልማት ይሰጧቸዋል። ነገር ግን እነዚህ ተሳታፊዎች የሰጧቸው መልሶች በአብዛኛው ትክክል ያልሆኑትን ነው።
ለተወሰኑት ተሳታፊዎች ደግሞ፤ ምንም እንኳን ብዙዎችን በትክክል ቢመልሱም፥ ብዙ እንደተሳሳቱ በመንገር ጥቂት ይሰጧቸዋል ወይም ምንም አይሰጧቸውም።
ሁሉም ተሳታፊዎች ከቤተሙክራው ሲወጡ፤ በር ላይ እርዳታ የሚጠይቅ ሰው ይጠብቃቸዋል። የትኞቹ ብዙ ገንዘብ የሚለግሱ ይመስሏቸዋል?
ብዙ ተሳስተው እያለ ብዙ እንደመለሱ ያህል ብዙ ገንዘብ የተሰጣቸው (ያገኙት ገንዘብ በጉብዝናችን ነው ብለው የሚያምኑት)?
ወይስ ብዙ መልሰው እያለ ጥቂት ያገኙት (ጥቂት ያገኘነው በራሳችን የእውቀት ማነስ ነው ብለው የሚያምኑት ወይም የእድል ጉዳይ ነው ብለው የሚያምኑት)?
እስቲ ገምት፤ የትኞቹ ብዙ የሚለግሱ ይመስልሃል?
የጥናቱ ውጤት እንደሚያሳየው፤ ሰዎች ያገኘነው ብዙ ገንዘብ የተለየ ብቃትና ጥረት ስላደረግን ነው ብለው ሲያምኑ፤ የበለጠ ንፉግ ይሆናሉ።
***
ዲበተን የሚባለው የፍልስፍና አስተማሪ ስለ ድሮዋ የእንግሊዝ ማህበረሰብና ስለ ዘመናዊ አሜሪካዋ ይናገራል። በድሮ እንግሊዝ ድሆች የሚባሉት ያልታደሉ ነው። ባለጠጎች ደግሞ የሚባሉት የታደሉት ነው። ባንድ ወቅት ያልታደለው በሌላ ጊዜ ሊታደል ይችላል። በአንድ ወቅት የታደለው በሌላ ጊዜ እድል ፊቷል ልታዞርበት ትችላለች። በዘመናዊ አሜሪካ ድሆች ተሸናፊዎች፥ ባለጠጎች ደግሞ አሸናፊዎች ይባላሉ። ሃብታሞች ራሳቸውን እንደ አሸናፊ በሚቆጥሩበት ማህበረሰብ፤ የበለጠ ንፉግ ይሆናሉ። ሃብታሞች ራሳቸውን እንደ እድለኞች በሚቆጥሩበት ማህበረሰብ፤ የበለጠ ቸር ይሆናሉ።
ባለጠጎች መንግሰሰማያት ከሚገቡ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ብታልፍ ይቀላል። የመንፈስ ድሆች መንግስተሰማያትን ይወርሳሉ።
እኔ የምለው ባለጠጎች ማለት ራሳቸውን አሸናፊዎች አድርገው የሚያስቡ ናቸው እንዴ?
እኔ የምለው የመንፈስ ድሆች ማለት ራሳቸውን እድለኞች፥ እግዜር በረከቱን ያፈሰሰባቸው አድርገው የሚቆጥሩ ናቸው?
እኔ ድሮም እጠረጥር ነበር። ችግራችን፤ እምነትን ባንድ ጎተራ፥ ህይወትን በሌላ ጎተራ ማስቀመጣችን ነው!!!!!
***
እና ዋናው ነጥብ ምንድን ነው? ለጋስነትን ለማበረታታት የሚያስችሉ መዋቅሮችን (እምነቶች፥ ህግጋት፥ ባህል፥ እሴቶች፥ ምህዳርና የመሳሰሉት) መዘርጋት ተገቢ ነው። እንደ ባህሪያችን ያንዱ የልግስና ድርጊት ሌሎቹም ለጋስ እንዲሆኑ የሚያደርግ ከሆነ፤ ልግስናን የሚገቱ ነገሮችን መቀነስ ይገባናል።
የአዲስ አበባ መስተዳድር ያወጣዋል የተባለው ህግ የሚያሰጋኝም በዚህ ምክንያት ነው። አንደኛ በአደባባይ ሰዎች እንዳይለግሱ በማድረግ፥ ልግስናን ጭራሽ እንዳያጠፋ ያሰጋል። ሁለተኛ ሌሎች ሲለግሱ አይቶ ይለግስ ለነበረ ሰው አሁን ላለመለገስ ምክንያት (ህግ አክባሪነት) የሚሰጥ ነው።
በእርግጥ ከዚህ በፊት እንደፃፍኩት ባልተማከለ በጎነት የመረጃ ችግሮች አሉ። ስለዚህ ለሃሳዊያን የተጋለጠ ነው። ለዚህ መፍትሄው ልመናን መከልከል ሳይሆን፤ የተማከለ በጎነትን ማበረታት ነው። የተማከለ በጎነት ማለት ሞኖፓላይዝድ ሞኖፓል ማለት አይደለም። የተገሩትን መርዳት የመንግስት ስራ መሆን ያለበት በተወሰነ ደረጃ ነው ብለው የሚሞግቱ ሰዎች አሉ። የጎዳና ተዳዳሪን፥ የሚበላው የሌለውን ሁሉ መንግስት መርዳት የለበትም። ይልቅስ ይሄን ስራ የሚሰሩ በጎአድራጎት ድርጅቶች እንዲደራጁ እድል መስጠት፥ መርዳት፥ መቆጣጠር ነው።
ለምሳሌ፤ በነፃ የማደሪያ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች እንዲኖሩ ማድረግ። እጅግ መሰረታዊ መጠለያ። እንዲሁም በእጅግ መሰረታዊ ቁርስ፥ እራት፥ ምሳ ከውሃ ወይም ሻይ ጋር በነፃ የሚያቀርቡ ድርጅቶች እንዲኖሩ ማድረግ።
እነዚህ ድርጅቶች ደግሞ ከሌሎች ሰዎች የገንዘብ እርዳታ እንዲቀበሉ ማድረግ።
ከአንድ ብር ጀምሮ በቀላሉ ገንዘብ የሚሰበስቡበት መንገድ መፍጠር። (ወይም) ወይም አሁን ከምናውቀው ብር የተለየ አይነት ገንዘብ መፍጠር። አሁን በምናውቀው ብር ስንፈልግ ቅቅል በቆሎ እንበላበታለን፥ ወይም እንጠጣበታለን፥ ወይም ደግሞ አጠራቅመን ላዳታክሲና ቤት እንገዛበታለን። የሃሳዊ ለማኞች ችግር፤ ስራ ማጣት፥ መራብና፥ መራዝ ሳይሆን፤ ስራ ሳይሰሩ ለመኖርና ለመበልፀግ የሚያደርጉት ሙከራ ከሆነ፤ የተሰጣቸውን ገንዘብ ለመጠጥና ቤትና መኪና ለመግዛት ያውሉታል የሚል ከሆነ፤ መፍትሄው፤ የተለየ የግብይት ገንዘብ ማስተዋወቅ ነው። ይሄ ገንዘብ የሚገዛው ነገር መሰረታዊ ምግብና መጠለያ ከተወሰኑ ቦታዎች ብቻ እንዲሆን ማድረግና ገንዘቡን ወደ መደበኛው ገንዘብ የሚቀየርበትን ስርአት በጥብቅ መከታተል ነው።
(“የፍቅር ሳንቲም” በሚል ከዚህ በፊት የፃፍኩትን ፅሁፍ ሌላ ጊዜ መልሼ እለጥፈዋለሁ።)
እንዲሁም ለእነዚህ ድርጅቶች ከአንድ ብር ጀምሮ ገንዘብ የሚሰጥ ሰው በይፋ የሚታወቅበት መንገድን መዘርጋት።
እንዲህ እንዲህ ስናደርግ፤
ልመናንና መስጠትን በህግ ሳንከለክል፥ የድርጊቶችን ማህበራዊ ትርጉም ሳናዛባ፤ ሃሳዊ ለማኞች ከገበያው ለቀው ይወጣሉ። የሚቀሩት ደግሞ የእውነት ችግርኞቹ ይሆናሉ።
**
ፌስቡክ እኮ የሚደብርህ ለዚ ነው። ከወራት በፊት የፆፍኩት ነገር ቁጭ ብሎ አገኘሁትና፣ አታፍርም ግን አንተ ባንድ ራስ ሁለት ምላስ ያለኝ መሠለኝ።
ያልተማከለ በጎነት
በነገራችን ላይ የማጅራት መቺና የኔቢጤዎች ጫና የበለጠ የሚወድቀዉ በማን ላይ ነዉ? በድሃዉ ወይስ በባለፀጋዉ? ከወርሃዊ ገቢ አንፃር፣ የበለጠ የሚመፀዉተዉ ማን ነዉ?
ይህን እንድል ያስገደደኝ፣ ብዙ ጊዜ የኔቢጤዎች የሚገኙት ታክሲና አዉቶብስ ተራ እና ቤተክርስቲያን አካባቢ ነው። በዚህ ደግሞ ከባለፀጎች ይልቅ ድሆች ይበዛሉ። ካላቸዉ ስለሚያካፍሉ ቢሆን እንጂ፣ ባይሆንማ በእነዜህ አካባቢ የኔቢጤም በጠፋ ነበር። ባለፀጎች ቤተክርስቲያን አይሄዱም፣ ቤተክርስቲያን ወደ ባለፀጎች ይሄዳል እያልኩ አይደለም።
በየቤቱ እየተዘዋወሩ ምፅዋት የሚለምኑ እንኳ፣ የባለፀጋ ቤት ማንኳኳት ይፈራሉ።
ይህንን እንደመነሻ አነሳሁት እንጂ፣ ዋናዉ ጉዳዩ ያልተማከለ በጎነት ላይ ነዉ? ከተማከለ እና ካልተማከለ በጎነት የትኛዉ ይሻላል?
ባልተማከለ በጎነት የመረጃ ችግር አለ። እዉነተኛዉን ከሃሰተኛዉ አይለይም። በመልክ እንኳ። እንኳን የኔቢጤዎች፣ የመፅሃፍ ቅዱስ አስተማሪዎች እንኳን በመልክና በታምራት አይለዩም። የመረጃ ችግር ሲኖር፣ እዉነተኛ የኔቢጤዎች በሃሰተኞቹ ተገፍተዉ እንደሚወጡ የኖቤል ተሸላሚዉ ኤኮኖሚስት ይናገራል፣ በሌላ መስክ።
እንዲሁም ሃሰተኞቹ ለማስመሰል በሚያደርጉት ዉድድር፣ የበለጠ አንጀት የሚበሉ ግጥምና ዜማዎች እና ዘግናኝ ቁስል መሳይ ኮስመቲክስ ይበዛሉ። ሲብስ ለልመና ለማሰማራት ብዙ ህፃናት ይበዛሉ። በህፃናት የሚፈፀም ወንጀል ይበዛል።
በየኔቢጤዎች መካከል የሚኖር ዉድድርና ትብብር በህግ ሰለማይገዛ የሃይል ተግባር ይጨምራል።
**
እውነት ግን እኔ አንድ ራስ ሁለት ምላስ ነኝ?
ወይስ አንድ ምላስ ብዙ ራስ?
ማንኛውም ድርጊት ማህበራዊ ትርጉም አለው።
መብላትንም ይጨምራል። የመብላት ተፈጥሯዊ ትርጉም ኤነርጂ ለስጋህ መስጠት ነው። ነዳጅ እንደ መቅዳት።
ግን ደግሞ የበላኽው ምግብ፥ ቤት፥ የከፈልከው ብር ደግሞ ማህበራዊ ትርጉም አለው። ለዛ እኮ ነው፤ በበውቀቱ ስዩም ወግ፤ ሰውዬው በረንዳ ላይ የሚበላው። በልቶ ማደሩን ማህበረሰቡ እንዲያውቅለት።
የሃንግሮኦስትሪያ ዜጎች/ተገዢዎች፤ ድንች አንበላም ብለው አስቸገሩ። የሆነ አስጠሊታ ድቡልቡል ነገር ብለው ተፀየፉት። (ተገዢ ሆነህ፤ መጠይፍ ይቻላል እንዴ? ብገዛም አይቆጨኝም!)
ንጉሱ ህግ አወጣ፤ “ድንች የልኡላን ቤተሰብ ምግብ ነው። ማንም መደበኛ ሰው ድንች ማብቀል፥ ማጓጓዝ፥ መነገድ፥ መቀቀል፥ መጥበስ፥ መላጥ፥ ማየት ((አቤት እኔ ማጋነን ስወድ)፥መመገብ አይችልም” የሚል ህግ።
የድንች ጥቁር ገበያ ተፋፋመ። ድንች በመብላት፤ የገዢነት መንፈስን መላበስ፤ ሁሉም ፈለገ።
አየህ፤ ህግ የድርጊቶችን ማህበራዊ ትርጉም ይቀይራል።
አታ ቱርክ ደሞ አለልህ። እንደሚባለው፤ አንድ ህግ አወጣ። አስገድዶ የደፈረ ሰው፤ ከመደበኛው ቅጣት በተጨማሪ፤ ሂጃም እንዲለብስ ይገደዳል። ማን ነው ታዲያ ሂጃም በፈቃዱ የሚለብሰው። ህግ የድርጊቶችን ማህበራዊ ትርጉም ይቀይራል።
በደቡባዊ አሜሪካ ግዛቶች፤ ነጭና ጥቁርን ለይቶ ማስተናገድ፤ ስር የሰደደ ማህበራዊ ግዴታ ነበር። አስበው አንተ ነጋዴ ሆነህ። አላማህ ትርፍ ነው። ጥቁሩም፥ ነጩም፥ ቢጫውም፥ አረንጓዴውም (ባንዲራችን ቢሆን እንዴት በፈነጠዝኩ) ገብቶ ከፍሎ ቢበላልህ፤ እንዴት በተደሰትህ። ብትፈቅድ ግን፤ ትገለላለህ። የዘርህ ከሃዲ ትባላለህ። እናማ፤ ህግ ወጣ። ልዩነትን ወንጀል የሚያደርግ። አሁን ሁሉንም ብታስገባ፤ ስግብግብ ከሃዲ ማንም አይልህም። ህግ አክባሪ ነው ትባላለህ። አየህ እንዴት ህግ የድርጊቶችን ማህበራዊ ትርጉም እንደሚቀይር።
የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር፤ ለለማኝ መስጠትን በህግ ሊከለክል ነው ሲባል፤አሃ አሁን የንፉግነት ትርጉም ተቀየር። ንፉግነት ህግ አክባሪነት ሆነ የሚባለው።
ይሄ ማለት፤ የመስተዳድሩ ልቦና ክፋት ሰንቋል ማለት አይደለም። እንደዛ አይደለም። ግን የመረጠው መሳሪያ ትክክል አይደለም እንደማለት ነው።
ችግራችን መቼ የቅናልቦና ማነስ ሆነና!
***
አዲስ አበባ ከተማ ያልተማከለ ፍቅር በህግ ሊከለክል ነው።
አጠገቤ ያሉ ሰዎች እያወሩ ነው። ለለማኝ እንዳትሰጡ ይላል አንዱ።
1000 ብር ያስቀጣል ይላል ሌላው።
እስርም አለው ይላል ሌላው።
ንፉግነት አዲስ ትርጉም አገኘ። ህግ አክባሪነት።
እውነተኛ ፍቅር ከዚህ በኋላ ሊታይ ነው!