ዛሬ በኢትዮጵያ የሁለት ወር ሕጻንን ጨምሮ 176 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል

ዛሬ በኢትዮጵያ የሁለት ወር ሕጻንን ጨምሮ 176 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዐታት ውስጥ  ለ4 ሺኅ 845 ሰዎች በተደረገ የላቦራቶሪ ምርመራ 179 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው እና ሁለት ሰዎች መሞታቸውን  የጤና ሚኒስቴር ገለፀ።
ዛሬ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው 116 ወንድና 63 ሴት ሲሆኑ ፣ የዕድሜ ክልላቸው ከ2 ወር ህጻን እስከ 80 ዓመት እንደሚደርስ የጠቆመው መግለጫ፤  በቫይረሱ ከተጠቁት ውስጥ 176 ሰዎች ኢትዮጵያዊያን፣ 3ቱ ደግሞ የውጭ ሀገር ዜጎች መሆናቸውንም አስታውቋል።
በጤና ሚኒስቴር መግለጫ ውስጥ ከተካተቱት ሰዎች መካከል፤ 111 ሰዎች ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ 15 ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል፣ 11 ሰዎች ከአፋር ክልል፣ 9 ሰዎች ከትግራይ ክልል፣ 5 ሰዎች ከሶማሌ ክልል፣ 2 ሰዎች ከደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል፣ 23 ሰዎች ከአማራ ክልል፣ 1 ሰው ከሐረሪ ክልል እንዲሁም 2 ሰዎች ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳዳር ነዋሪዎች እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል።
በተያያዘ ዜና ዛሬ የ2 ሰዎች ሕይወት እንዳለፈና ቫይረሱም በአስክሬን ምርመራ እንደተገኘባቸው የገለጸው የጤና ሚኒስቴር ዕለታዊ ሪፖርት፤  በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በቫይረሱ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 57 ደርሷል ብሏል።
በአንጻሩ በትላንትናው ዕለት 50 ሰዎች (41 ከአዲስ አበባ፣ 3 ከአፋር፣ 2 ሰዎች ከትግራይ ከሶማሌ እና 4 ሰዎች ከአማራ ክልል) ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 445 መድረሱን መረዳት ተችሏል።

LEAVE A REPLY