ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ሀገራዊ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት ነገ የሀገር ሽማግሌዎች ቡድን ወደ ትግራይ ክልል ይጓዛል።
52 አባላትን ያካተተው የሀገር ሽማግሌዎች ልዑክ ወደ መቀሌ የሚያደርገው ጉዞ በአገሪቱ ያለውን የፖለቲካ ውጥረት ለማርገብ ያለመ መሆኑን የሚያስረዳው ዜና፤ በቡድኑ ውስጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያሪክ አባ ማቲያስ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እንድሪስ እና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ እየሱስ ሱራፌልን ጨምሮ የሠባት የኃይማኖት ተቋማት መሪዎች ተሳታፊዎች እንደሚሆኑ ያስረዳል።
የሰላም ልዑካን ቡድን ከሃይማኖት መሪዎቹ በተጨማሪ፣ የሀገር ባለውለታ የሆኑ ታዋቂ ሰዎችና የሀገር ሽማግሌዎች በቡድኑ ውስጥ እንደሚሳተፉ፣ የጉዞው ሐሳብ አመንጪና አስተባባሪ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ስለመሆኑም ተነግሯል።
የቡድኑን የጉዞ ወጪ አጠቃላይ ሙሉ ወጪው ጉዳዩ ያገባናል፣ ሰላም እንወዳለን ባሉ ባለሀብቶች የተሸፈነ ሲሆን፣ በዚህ መልክ ተሳትፎ ካደረጉት መሀል ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሤ የልዑካን ቡድኑን የመጓጓዣ ወጪ እንደሸፈነ (እርሱም የቡድኑ አባል ነው) የሚያስረዳው ዜና በዶክተር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው የትግራይ ክልል መንግሥትም ነገ እንግዶች እንደሚመጡበት ከወዲሁ እንዲያውቅ ተደርጓል ሲል አስታውቋል።
በተለያዮ ታዋቂ ሰዎች የተሞላው ቡድን ነገውኑ ጉዳዩን ጨርሶ የሚመለስ ሲሆን፣ የሃይማኖት አባቶቹና የሀገር ሽማግሌዎቹ ለተመሳሳይ ተልዕኮ በቀጣይም ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የመጓዝ ዕቅድ እንዳለው ተሰምቷል።