ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ከጥቂት ሳምንታት በፊት ” በሀገሬ አንድም የኮሮና በሽተኛ የለም፣ ተይዘው የነበሩትም አገግመዋል” ያለው የኤርትራ ጤና ሚኒስቴር በኮቪድ-19 መያዛቸው የተረጋገጡ 31 ሰዎች አግኝቻለሁ ሲል ገለፀ።
31ዱ ሰዎች የተገኙት የአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ጊዜያቸውን ካጠናቀቁ በኋላ መሆኑን የገለፀው ሚኒስቴሩ፤ ቫይረሱ የተገኘባቸው 30 ሰዎች በቅርቡ ከሱዳን የተመለሱ ኤርትራውያን መሆናቸውን፣ አንደኛው ግለሰብ ደግሞ ከኢትዮጵያ የተመለሰ ኤርትራዊ ነው ብሏል።
ምንም እንኳን የእንቅስቃሴ ገደብ በቀጠናው ባሉ አገራት ቢጣልም፤ ባለፉት ሁለት ወራት 7 ሺኅ 158 የሚሆኑ ኤርትራውያን ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ ከኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ጅቡቲ እና የመን ወደ ኤርትራ መመለሳቸውን መግለጫው ጠቁሟል።
በመላው ኤርትራ በሚገኙ 47 ለይቶ ማቆያዎች ውስጥ 3 ሺኅ 135 ሰዎች ይገኛሉ ያለው ሚኒስቴሩ፤ እስከ ዛሬ ድረስ ኤርትራ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡ 96 ሰዎች ማግኘቷን፣ ከእነዚህም መካከል 57ቱ በጤና ማዕከላት ውስጥ ክትትል እየተደረገላቸው ሲሆን፣ 39 ሰዎች ከበሽታው ሙሉ ለሙሉ ማገገማቸውን አስታውቋል።