የመጠባበቂያ ነዳጅ በሱሉልታ ዴፖ ማከማቸት ተጀመረ 

የመጠባበቂያ ነዳጅ በሱሉልታ ዴፖ ማከማቸት ተጀመረ 

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ኢትዮጵያ በሱሉልታ ዴፖ በመጠባበቂያነት የምትይዘውን ነዳጅ ካለፈው ሃሙስ አንስቶ ማስገባት ጀምራለች ተባለ።

እየገባ ያለው ነዳጅ እጥረት ሲያጋጥም ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን፣ በሱሉልታ ዴፖ በአጠቃላይ 60 ሺኅ ሜትር ኪዩብ ወይም 60 ሚሊየን ሊትር ነዳጅ በመጠባበቂያነት የመያዝ ዕቅድ መያዙ በመነገር ላይ ነው።
በዕቅድ ከተያዘው ውስጥ የተወሰነው ካለፈው ሀሙስ አንስቶ፣ ከጁቡቲ ወደብ ወደ መሀል ሀገር እየተጓጓዘ መሆኑን በኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት፣ የአቅርቦት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አባይነህ አወል አስረድተዋል።
የሚከማቸው ነዳጅ እንደሚታየው የአቅርቦት መስተጓጐል ሲያጋጥም ለአዲስ አበባና ሌሎች አካባቢዎች ነዳጁ ይሰራጫል ተብሏል።
የኢትዮጵያ አጠቃላይ ዓመታዊ የነዳጅ ፍጆታዋ ወደ አራት ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ነው የሚሉት አቶ አባይነህ አወል፤ ቨከኮሮና ቫይረስ በወረርሽኝ መልክ መከሰት አስቀድሞ ይህ ፍላጎት በጁቡቲ እና በሱዳን በኩል በሚገባ ነዳጅ ይሸፈን እንደ ነበርም ገልፀዋል።
አሁን ኢትዮጵያ ነዳጅ እያስገባች ያለችው በጁቡቲ በኩል ብቻ ነው፤ የእዚህ ምክንያቱ ሱዳን በቫይረሱ ስጋት ምክንያት ድንበሯን በመዝጋቷ መሆኑም ተሰምቷል።
ሀገሪቱ ድንበሩን ለነዳጅ ማስገባቱ ሥራ ክፍት እንድታደርግ የማግባባቱ ሥራ እንደቀጠለ እንደሆነ የሚያመላክተው መረጃ፤ በሱዳን በኩል የሚገባው ነዳጅ ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ፍላጎት 20 በመቶው እንደነበርም ያስረዳል።

LEAVE A REPLY