ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የሠባት ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች በግንባታ ላይ ያለውን የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉብኝት አደረጉ።
በኢኖቬቭንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ኢንጂነር አብርሃም በላይ እና በተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻ የተመራው ቡድን ግድቡ ያለበትን የግንባታ ሂደት በጥልቀት ጎብኝተዋል።
በግድቡ ላይ ስለተከናወኑት ተግባራትና በመጪው ክረምት ውሃ ለመያዝ የሚሠሩትን ሥራዎች በተመለከተ ለርዕሰ መስተዳደሮቹ ገለጻ ያደረጉላቸው ኢንጂነር አብርሃም በላይ፤ ትልልቅ ሥራዎች በሚሠሩበት ወሳኝ ምዕራፍ ጊዜ ላይ ርዕሰ መስተዳድሮቹ ግድቡን መጎብኘታቸው የተለየ ትርጉም እንደሚሰጠው ተናግረዋል።
የግድቡ ወቅታዊ የግንባታ ሂደት አበረታች እንደሆነ መመልከታቸውን ያረጋገጡት ርዕሰ መስተዳድሮቹ፤
ጉብኝቱ ስለግድቡ ለሚመሩት ሕዝብ በተገቢው ሁኔታ ለመግለፅ እና በተለያዩ ወገኖች የሚሰነዘሩ አሉታዊ አስተያየቶችን ለማክሸፍ እንደሚያስችላቸው ገልፀዋል።
ግንባታው እየተፋጠነ የሚገኘው የህዳሴው ግድብ የመሀከለኛው ክፍል የኮንክሪት ሙሌት ለዓመታት ከነበረበት ከባህር ጠለል በላይ ከ525 ሜትር አሁን ላይ 552 ሜትር እንደ ደረሰና ውኃ ለመያዝም ስምንት ሜትሮች ብቻ የቀረው መሆኑ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ይፋ አድርጓል።