የኮቪድ 19 ቫይረስ ያለበት ሰው የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒትን ለሚፈልጉ ኢንፌክሽኖች ይጋለጣል ተባለ

የኮቪድ 19 ቫይረስ ያለበት ሰው የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒትን ለሚፈልጉ ኢንፌክሽኖች ይጋለጣል ተባለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ከመከላከል ጎን ለጎን የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒት በጀርሞች እንዳይላመዱ ጥንቃቄ እና ቁጥጥር  ሊደረግ ይገባል።

“የፀረ-ተህዋሲያን ብግርነትን መቆጣጠር እና መከላከል በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት” በሚል መሪ ሐሳብ በሀገር ዐቀፍ ደረጃ ለስምንተኛ ጊዜ ዛሬ በተከበረበት ወቅት፤ የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች መላመድ ዓለማችንን ከሚያሰጓት የጤና ችግሮች አንዱ መሆኑን ተነግሯል።
በዓለም ላይ በየዓመቱ ከ750 ሺኅ በላይ ሰዎች በዚህ ችግር ይሞታሉ የሚለው ጥናት፤ በተለይ እንደ ቲቢ፣ ወባ፣ ኤች አይቪ/ኤድስ ባሉ በሽታዎች በስፋት የሚጠቁት ታዳጊ አገሮች ደግሞ የችግሩ ዋነኛዎቹ ገፈት ቀማሾች እንደሚሆኑ አመላክቷል።
ከዚህ አኳያ የችግሩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ ያስገባ አፋጣኝ እርምጃ ካልተወሰደ ፣ የሰው ሕይወትን ከመቅጠፉ ባሻገር በአገር ኢኮኖሚ ላይም ጫና ያስከትላል ያሉት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ የኮሮና ቫይረስ የተገኘበት ግለሰብ የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒትን ለሚፈልጉ ኢንፌክሽኖች የመጋለጡ ዕድል ከፍተኛ ነው ሲሉም ተደምጠዋል።
በእንዲህ ዓይነቱ ወቅት ተገቢውን ጥንቃቄ  ካልተደረገ መድኃኒት ጀርሞች እንዲላመዷቸው በማድረግ አሳሳቢ የጤና እክል ስለሚያስከትል፣  መድኃኒቱ በሐኪም ትእዛዝ ብቻ ሊወሰድ እንደሚገባም ሓላፊዋ አሳስበዋል።
የፀረ ተህዋሲያን መድኃኒት በጀርሞች መላመድ እና የኮሮና ቫይረስ ተመሳሳይ ባሕርይ አላቸው እንዳላቸው ያመላከቱት የኢትዮጵያ ፋርማሲ ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ መስፍን ጉጂ ፤ “ሁለቱንም የጤና ችግሮች አስቀድመን መከላከል ካልቻልን በመድኃኒት ሕክምና የማዳኑ ሥራ ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራሉ” ብለዋል።

LEAVE A REPLY