176 ሰዎች በኮሮና ሲያዙ፣ ሦስት ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል

176 ሰዎች በኮሮና ሲያዙ፣ ሦስት ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዐታት ውስጥ  ለ5 ሺኅ 636 ሰዎች በተደረገ የላቦራቶሪ ምርመራ 176 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው እና የሦስት ሰዎች ሕይወት እንዳለፈ የጤና ሚኒስትር አስታወቀ።

በወጣው መግለጫ መሠረት በአጠቃላይ በሀገሪቱ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 3 ሺኅ 521 መድረሱ ተሰምቷል።
ዛሬ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው 116 ወንድና 60 ሴት ሲሆኑ፣ የዕድሜ ክልላቸው ከ5 ወር ህጻን እስከ 90 ዓመት ይደርሳል ያለው የጤና ሚኒስቴር፤ ከእነርሱ ውስጥም 175 ሰዎች ኢትዮጵያዊያንና አንድ የውጭ ሀገር ዜጋ መሆናቸውን አስታውቋል።
በምርመራ ኮቪድ 19 ቫይረስ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 98 ሰዎች ከአዲስ አበባ፣ 3 ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል፣ 2 ሰዎች ከአፋር ክልል፣ 31 ሰዎች ከትግራይ ክልል፣ 7 ሰዎች ከሶማሌ ክልል፣ 33 ሰዎች ከአማራ ክልል እንዲሁም 2 ሰዎች ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተገኙ መሆናቸውም ተገልጿል።
በሌላ በኩል ዛሬ ሦስት ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ያለፈ ሲሆን፣ ሁለቱ ሰዎች የሕክምና ዕርዳታ ሲደረግላቸው የቆዩ፤ አንድ ሰው ደግሞ በአስክሬን ምርመራ ቫይረሱ እንደተገኘበት የጠቆመው የጤና ሚኒስቴር፤ ይህን ተከትሎ አጠቃላይ በኢትዮጵያ በቫይረሱ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 60 መድረሱን አረጋግጧል።
በተያያዘ ዜና ትናንት75 ሰዎች (31 ከአዲስ አበባ፣ 28 ሰዎች ከሱማሌ ክልል፣ 10 ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል፣ 1 ሰው ከአፋር፣ 5 ሰዎች ከአማራ ክልል) ከበሽታው ያገገሙ መሆኑን ተከትሎ በአጠቃላይ በሀገሪቱ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 620 ደርሷል፡፡
በኢትዮጵያ በዚህ ወቅት 2ሺኅ 839 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸው የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ሲሆን፣ 29 ሰዎች በጽኑ ሕክምና ክትትል ክፍል ይገኛሉ።

LEAVE A REPLY