ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ሰሞኑን የኦሮሚያ ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎች አንድ የሳር ክዳን ጎጆ ቤትን ሲያቃጥሉ የሚያሳያውን ተንቀሳቃሽ ምስል እያጣራ እንደሚገኝና ድርጊቱ እርሱን እንደማይወክል ገለፀ።
ድርጊቱ የት፣ መቼ እና በማን እንደተፈጸመ የሚያጣራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ጉጂ ዞን ተልኳል ያሉት የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ገላን፤ ካለፉት ሥድሥት ወራት ወዲህ በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ የሚታየውን ዓይነት የደንብ ልብስ የኦሮሚያ ክልል ጸጥታ ኃይል አባላት እንደማይለብሱ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
“የጸጥታ ችግር ባለባቸው በወለጋ፣ በጉጂ እና በቦረና ዞኖች ይህን አይነት (ሽሮ መልክ ያለው ቡራቡሬ የፖሊስ የደንብ ልብስ) እንዳለይለበስ ሲል የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ከሥድሥት ወራት በፊት መመሪያ አስተላልፏል” የሚሉት ኮሚሽነሩ ፤ “ይህን ዩኒፎርም በብዛት እየለበሱ ያሉት የሸኔ ታጣቂዎች ናቸው። በተለይ ደግሞ በጉጂ ዞን ውስጥ ይህን እየለበሱ ያሉት የሸኔ አባላት ናቸው። በመሆኑም የጸጥታ ኃይሎች በአካባቢው የሚለብሱት የደንብ ልብስ ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል” ሲሉ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አሁን ላይ የተለቀቀው ቪዲዮ የቆየ ከሆነ በሚል አጣሪ ቡድን ወደ ስፍራው መላኩንና ውጤቱ ሲታወቅ ይፋ እንደሚደረግ የገለፁት ኮሚሽነሩ፤ እስከዚያ ድርጊቱን ሲፈጽሙ የታዮት ሰዎች የኦሮሚያ ፖሊስ አባልናቸው ወይም አይደሉም ማለት እንደማይቻልም ገልፀዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ላይ በጉጂ ዞን ውስጥ ተፈጸመ በተባለው እርምጃ፤ “የሸኔ አባል ቤት ነው” የተባለ የሳር ክዳን ቤት ፤ የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት የደንብ ልብስን በለበሱ እና የአካባቢው ሚሊሻ ናቸው በተባሉ ሰዎች ሲቃጠል የሚያሳየው ቪዲዮ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየታየ ይገኛል።
እስካሁን ምሰሉ የት እና መቼ እንደተቀረጸ፣ እንዲሁም የሳር ክዳን ቤቱ እንዲቃጠል የተደረገው በየትኛው አካል እንደሆነ፣ እና የቤቱ ባለቤት ማን እንደሆነ በገለልተኛነት ያረጋገጠ አካልም አልተገኘም።
ሠባት ደቂቃ በሚወስደው ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ ቁጥራቸው ከ10 በላይ የሚሆኑና ሽሮ መልክ ያለው ቡራቡሬ የፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎች፣ የሳር ክዳኑን ቤት ሲያቃጥሉ፤ እንዲሁም ቁጥራቸው አነስ ያለ፣ ሙሉ በሙሉ አረንጓዴ ዩኒፎርም የለበሱ እና የታጠቁ ሰዎች ሰዎች ቆመው ሲመለከቱ በግልፅ ያሳያል።