ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ኢትዮጵያ ውስጥ ኮሮና ከገባ በኋላ በቫይረሱ ተይዘው ካገገሙ ሰዎች መሀል በአንድ ቀን ከፍተኛ ሰዎች ማገገማቸው ታወቀ።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ሥር በሚገኘው የሚሊኒየም ማገገሚያ ማዕከል ውስጥ ከኮቪድ-19 ያገገሙ 87 ሰዎች ከማዕከሉ መውጣታቸውም ተነግሯል።
በአሁኑ ወቅት በማዕከሉ ውስጥ 656 ኮሮና ቫይረስ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ሕክምናቸውን እየተከታተሉ መሆኑን የገለፁት የማዕከሉ ክሊኒካል ዳይሬክተር ዶክተር ውለታው ጫኔ፤ ከነዚህ ውስጥ 157 ሰዎች የመጀመሪያ የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤታቸው ከኮሮና ቫይረስ ማገገማቸውን የሚያረጋግጠውን (ኔጋቲቭ ) ያሳየ መሆኑን ተከትሎ 87 ሰዎች ዛሬ ከማዕከሉ እንዲወጡ ተደርጓል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ የኮቪድ-19 ሕክምና ማዕከል ሆኖ ህሙማንን መቀበል የጀመረው ከግንቦት 25 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ነበር። ማዕከሉ 40 የጽኑ ሕሙማን መኝታዎችና 1 ሺኅ ጽኑ ያልሆኑ ሕሙማን ታካሚዎች አገልግሎት መስጠት የሚችል ከመሆኑ በተጨማሪ የላቦራቶሪ፣ የመድኃኒት ቤት፣ የጤና ባለሙያዎች ልብስ መቀየሪያ፣ መታጠቢያዎችና ሌሎች ክፍሎችን አሟልቶ ይዟል።
ትናንት የተመዘገበውንና ከፍተኛ የሆነውን በመላ ሀገሪቱ ያገገገሙ 118 ሰዎችን ተከትሎ በኢትዮጵያ ኮሮና ቫይረስ በምርመራ ከተገኘባቸው ሰዎች ውስጥ እስከ አሁን 620 ሰዎች ማገገማቸው ተነግሯል።