ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ በቁም እስር ላይ የሚገኙት የሼህ ሞሐመድ ሁሴን አልአሙዲ ቀኝ እጅ የሆኑት አቶ አብነት ገብረ መስቀል፤ የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው መሾማቸው ተሰማ።
የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ባለቤትና ሊቀመንበር ሼክ መሐመድ ሑሴን አሊ አል አሙዲን፣ አቶ አብነት ገብረመስቀልን የሚድሮክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አድርገው እንደሾሟቸውም አዲሱ ተሿሚ አቶ አብነት ለመገናኛ ብዙኃን አረጋግጠዋል።
የጥምር ዜጋ ባለሀብቱ የቅርብ ወዳጅ አቶ አብነት ገብረ መስቀል በሚድሮክ ኢትዮጵያ ጥላ ስር የሆኑትን የኮንስትራክሽን፣ የሆቴል፣ የሪል ስቴትና የመድኃኒት ኩባንያዎችን በበላይነት እንዲመሩ ከፍተኛ ሓላፊነት ተሰጥቷቸዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎንጰአቶ ጀማል አሕመድ በእርሻ፣ በማዕድን፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በአዲስ ሆምዴፖ ሥር ያሉትን ኩባንያዎች እንዲመሩ ሲሾሙ፤ አቶ ደረጀ ኢየሱስወርቅ የሬይንቦ አየር መንገድ፣ የመኪና ኪራይና አስጎብኚ ድርጅትን እንዲሁም አቶ ኃይሌ አሰግዴ ሲመሩ በቆዩት የደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ ኃላፊነት እንዲቀጥሉ መደረጋቸውን አቶ አብነት ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ ሠፊ ተሳትፎ ያለውጰየሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕን በዋና ሥራ አስፈፃሚነት ለ20 ዓመታት ያገለገሉት ዶ/ር አረጋ ይርዳው ባለፈው ሚያዚያ 19 ቀን 2012 ከሓላፊነት መነሳታቸውና፣ በእርሳቸው ቦታ አቶ ጌታቸው ሐጎስ በጊዜያዊነት ተሹመው እንደነበር አይዘነጋም።