የህዳሴው ግድብ የቅድመ ኃይል ማመንጫ ተርባይን ሥራዎች መጠናቀቃቸው ተነገረ

የህዳሴው ግድብ የቅድመ ኃይል ማመንጫ ተርባይን ሥራዎች መጠናቀቃቸው ተነገረ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የህዳሴ ግድብ ቅድመ ኃይል ማመንጫ የሁለት ጀነሬተር ተርባይን ሥራዎች ተጠናቅቀው በኮንክሪት እየተሞሉ መሆናቸው ተነገረ።

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ የተከናወኑ ሥራዎች ሲመዘኑ በ2012 ዓ.ም የላቀ ሥራ መሠራቱንና ግንባታው በሁሉም መስክ የተሳካ የሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የገለፁት የታላቁ የህዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ፤ ፕሮጀክቱ በሙሉ አቅም በሁሉም አቅጣጫ በሦስት ሽፍት እየተሠራ ነው ብለዋል።
 የግድቡ የሲቪል ኢንጅነሪንግ ሥራ 87 በመቶ፣ የብረታ ብረት ሥራዎቹ ደግሞ ከ31 በመቶ በላይ፣ የኤሌክትሮ ሜካኒካል የተርባይንና የጀነሬተር ሥራዎች አፈጻጸምም 45 በመቶ ተሠርተው በተሳካ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።
ቀደም ባሉት ዓመታት ችግር የነበረባቸው የቅድመ ኃይል ማመንጫ የብረታ ብረት ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ተነስተው በአዲስ መተካታቸውን የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፤ የግድቡ የግርጌ የውኃ ማስተንፈሻ፣ እንዲሁም ከቅድመ ኃይል ማመንጨት ጋር የተገናኙ የሁለት ጀነሬተር ተርባይን ሥራዎች ተጠናቅቆ በኮንክሪት እየተሞሉ ይገኛሉ ብለዋል።
የዐሥራ አንዱ ቀሪ ዩኒቶች የብረታ ብረት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነና ሌሎች ለሲቪል ኮንትራክተሮች የተሰጡ ሥራዎች ደግሞ በቅርቡ እንደሚጀመሩም በመነገር ላይ ነው።
በተጨማሪም ለሁለቱ ቅድመ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የሚሆን የብረታ ብረት ሥራዎች ተከናውነው ኮንክሪት እየተሞሉ መሆኑንም በቀጣይም የጀነሬተር ተርባይን ተከላ እንደሚጀመር ገልጸዋል። በግድቡ በተለይም የመካከለኛው ውኃ ይፈስበት የነበረው ቦታ ርዝመቱ 525 ሜትር የነበረ ሲሆን፣ እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ድረስ 560 ሜትር ለማድረስ ከፍተኛ ሥራ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ፤ ጎንና ጎኖቹም በኮንክሪት እየተሞሉ መሆኑንና የግድቡ ሥራ ከተጀመረ አንስቶ እንደዚህ ዓመት በሁሉም አቅጣጫ በሙሉ አቅም የተሠራበት ጊዜ እንደሌለም ጭምር አስረድተዋል።
የግድቡ ግንባታ በሁሉም መስክ የተሳካ የሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የገለፁት ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ “በኤሌክትሮ ሜካኒካሉም፣ በሲቪሉም፣ በብረታ ብረት ሥራውም በሦስት ሽፍት ያለ እረፍት እየተሠራ ነው፤ ይህም በጣም አስደሳችና እስከ ዛሬ ያልተሰራበት አካሄድ ነው” ብለዋል።

LEAVE A REPLY