የአዲስ አበባው ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ስያሜውን እንዲሰርዝ በፍርድ ቤት ተወሰነበት

የአዲስ አበባው ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ስያሜውን እንዲሰርዝ በፍርድ ቤት ተወሰነበት

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ባለፉት ዓመታት ከተገነቡና በአጭር ጊዜ ውስጥ ስኬታማ ለመሆን ከቻሉ በርካታ ሆቴሎች መሀል አንዱ የሆነው የአዲስ አበባው ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል፤ ስያሜውን እንዲሰርዝ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተወስኖበታል።

የአዲስ አበባው ኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል ስሙን ያለ ፈቃድ በመጠቀሙ፣ ለዓለም ዐቀፉ የኢንተርኮንትኔንታል ኮርፖሬሽን የ13 ዓመት ሮያሊቲ ወይም ስሙን በመጠቀም የሰበሰበውን ገንዘብ እንዲከፍል በፍርድ ቤት የተወሰነበት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
ባለ አምስት ኮከብ  ነው የተባለው የአዲስ አበባው ኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል ከእንግዲህ ስያሜውን  መጠቀም እንዲያቆምም ፍርድ ቤቱ ጥብቅ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
የአዲስ አበባው ኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል እስከዛሬ ስያሜውን ያለ ፈቃድ በመጠቀሙ ሳቢያ ለዓለም ዐቀፉ የኢንተርኮንትኔንታል ኮርፖሬሽን ሮያሊቲ ከፍተኛ መጠን ያለው ዶላር ሊከፍል እንደሚችል ከወዲሁ እየተነገረ ነው።
የአዲስ አበባው ሆቴል በስሙ የከፈተውን ድረ ገጽ እንዲዘጋ፣ ማንኛውንም ማስታወቂያዎች እንዲያነሳ መወሰኑንም የዓለም ዐቀፉ ኢንተርኮንትኔንታል ሆቴልስ ኮርፖሬሽን ጠበቃ አቶ ኢዮብ ሐጎስ ለሸገር ራዲዮ ሲገልፁ ተደምጧል።
ባለፈው ዓመት በዓለም ዐቀፉ ኢንተርኮንትኔንታል ኮርፖሬሽን አሸናፊነት ሆቴሉ ስያሜውን እንዲሰርዝ መወሰኑ ሲወሰን፤ ሆቴሉ ይግባኝ ቢጠይቅም፣ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም የሥር ፍርድ ቤቱን ውሳኔ  እንዳፀናው ለማወቅ ተችሏል፡፡
ዓለም ዐቀፉ ኢንተርኮንትኔንታል ኮርፖሬሽን ከስምንት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ በንግድ ምልክት ባለቤትነት መመዝገቡን መረጃዎች ያሳያሉ።

LEAVE A REPLY