ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ በአየር ትራንስፖርት ዘርፉ ላይ በተፈጠረው መስተጓጎል ምክንያት አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ አጥቷል ተባለ።
የኮሮና ቫይረስ ዓለም ዐቀፍ ወረርሽኝ በአየር መንገዶች ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ቀውስ ማስከተሉን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ገልፀዋል።
ከ90 በመቶ በላይ የመንገደኛ በረራዎች መቆማቸውን ተከትሎ ከየካቲት እስከ ሰኔ መጨረሻ ድርጅቱ መንገደኛ በማጓጓዝ ሊያገኘው ይገባ የነበረው ወደ አንድ ቢሊየን ዶላር ገቢ ሳያገኝ መቅረቱን ከሥራ አስኪያጁ ገለጻ መረዳት ተችሏል።
የኮቪድ 19 ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ የዓለም አንድ ሦስተኛ የሚሆነው ሕዝብ ከቤቱ እንዳይወጣ ከተደረገ ወራት በማለፋቸው በአየር የሚደረግ ጉዞ ሙሉ በሙሉ ቆሟል። ይህም በአየር መንገዶች ዓይን በሚታይበት ወቅት በአሁን ሰዓት ብዙ አየር መንገዶች አውሮፕላኖቻቸውን እንዲቆሙ አስገድዷል ተብሏል።
“የመንገደኛ በረራ ቆሟል። በኢትዮጵያ አየር መንገድም ከ90 በመቶ በላይ የመንገደኞች አውሮፕላኖቻችን ቆመዋል። ይሄ ለአንድ አየር መንገድ እጅግ በጣም ትልቅ የፋይናንስ ቀውስ ነው የሚያመጣው። ይህም ምንም የሚካድ አይደለም እጅግ ተጎድተናል” ያሉት አቶ ተወልደ ገ/ማርያም፤ የዚያን ያህል ደግሞ አየር መንገዱ ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ የሚያኮራ ሥራ ሠርቷል ሲሉም ተደምጠዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቢበርም ባይበርም በወር አምስት ቢሊየን ብር እንደሚያወጣ የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ከመጋቢት ወር ጀምሮ የመንገደኞች ጉዞ በሚቆምበት ጊዜ የድርጅቱን ቋሚ ወጪዎች ለመሸፈን፣ አውሮፕላን ለመግዛት የተበደረውን ብድር ከነወለዱ መመለስ ይጠበቅበታልም ብለዋል።
በተያያዥ አውሮፕላኖችን የተከራየንበት ወርሃዊ የኪራይ ወጪ ለመክፈል፣ እንዲሁም የሠራተኛ ደሞዝ፣ ጥቅማጥቅም፣ አበል፣ ለመሸፈን የሚያስችለውን “በየወሩ አምስት ቢሊየን ብር በየወሩ እንዴት ነው የምናገኘው? ይህ ወረርሽኝ ከቀጠለስ ምን እናደርጋለን?” በማለት ጥልቅ ውይይት ተደርጎ ከመንገደኛ ማጓጓዝ ባሻገር ያለውን እድል በመፈተሽ፣ የጭነት አገልግሎት መስጠትን በወቅቱ የተገኘ ጥሩ አማራጭ ተደርጎ መወሰዱን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል።