ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በ2012 በጀት ዓመት 11 ወራት ውስጥ ወደ ውጪ ከተላከ የሥጋና ወተት ምርት 68.13 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴር መ/ቤቱ የሥጋና ወተት ኢንስቲትዩት የ2012 በጀት ዓመት የ11 ወራት የኤክስፖርት አፈፃፀምን በዘርፉ ከተሰማሩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ዛሬ በሠፊው ገምግሟል።
ከሥጋና ወተት 113.81 ሚሊያን ዶላር ገቢ በበጀት ዓመቱ 11 ወራት ለማግኘት ታቅዶ፣ 68.13 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ሲገኝ፣ ከበግና ፍየል ሥጋ 61.31 ሚሊዮን ዶላር፣ ከዳልጋ ከብት 1.3 ሚሊዮን ዶላር፣ ከእንስሳት ተረፈ ምርት 2.93 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ከማር፣ ከሰም፣ ከዓሳ ምርት እና ከወተት 2.60 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደተገኘ በግምገማው ላይ የቀረበው ሪፖርት ያሳያል።
የእርድ እንስሳት አቅርቦት ጥራት ችግር፣ የእንስሳት ማቆያ እጥረት፣ የብድር አቅርቦት እጥረት፣ ህገ-ወጥ የቁም እንስሳት ንግድና የመብራት መቆራረጥ ምክንያት የተያዘውን እቅድ ሙሉ በሙሉ መፈጸም እንዳይቻል አድርጓል ያሉት የሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲቱት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ጋሹ፤ እነዚህ ነገሮች ከተስተካከሉ የበለጠ ውጤት ማምጣት ይቻላል ብለዋል።
በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የንግድ ማስፋፊያ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ ፤ ከሚፈለገው አካል ያለመድረስ እንጂ የአቅርቦት ችግር የለም ካሉ በኋላ፤ በአቅራቢዎችና በቄራዎች መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት እንዲኖር፣ የአቅርቦት ሰንሰለቱን ማሳጠር ያስፈልጋል ብለዋል።