ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በኢትዮጵያውያን እየተገነባ ያለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያውያን አልፎ ለቀጠናው የኢኮኖሚ ውህደት ጠቃሚ መሆኑን ኬንያ አስታወቀች።
የኬንያ ፓርላማ አፈ ጉባዔ ጀስቲን ሙቱሪ ዛሬ በኬንያ አምባሳደር መለስ ዓለምን በጽ/ቤታቸው ባነጋገሩበት ወቅት በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚካሄደው ድርድር ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበትና በሰጥቶ መቀበል መርህ ሊካሄድ የሚገባው እንደሆነ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን እንደሌሎች የአካባቢው ሀገሮች የተፈጥሮ ሀብታቸውን በመጠቀም የመልማት ተፈጥሮአዊ መብት እንዳላቸው እገነዘባለሁ ያሉት አፈ ጉባዔው፤ የህዳሴውን ግድብ ጅምር ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ማንንም በማይጎዳ መልኩ ከዳር እንደምታደርሰው ገልፀዋል።
በውይይቱ በኢትዮጵያ እና ኬንያ ፓርላማዎች መካከል በተለያዩ ክፍለ-አህጉራዊ እና ዓለም ዐቀፋዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ ተደጋግፎ ለመሥራት ከመግባባት መድረሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።