ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የህወሓት ሊቀ መንበር ዶክተር ደብረፂዮን የህዳሴው ግድብ እንዲጓተትና ሀገሪቱም ለኪሳራ እንድትዳረግ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል ተባለ።
የቀድሞው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አለማየሁ ተገኑ “የህዳሴ ግድቡ ግንባታ በወቅቱ የቦርዱ ሰብሳቢ በነበሩት ዶክተር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል አድራጊ ፈጣሪነት በፍጥነት ተዳክሞ ለከፍተኛ ኪሳራ ተዳርጓል” ሲሉ እውነታውን ገሀድ አውጥተዋል።
አሁን በሩሲያ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለ ሙሉ ሥልጣን አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ የህዳሴ ግድቡ አቶ መለስ ዜናዊ በሕይወት እስከ ነበሩበት ጊዜ ድረስ በየወሩ ይገመገም እንደነበርና ከእርሳቸው ሕልፈት በኋላ በየወሩ መገምገሙ መቅረቱን ገልፀዋል።
በጊዜው የቦርዱ ሰብሳቢ በክላስተር አደረጃጀት በሁለት ወር አንድ ጊዜ እንዲታይ አቅጣጫ ቢያስቀምጡም ሰብሳቢው አሠራሩን ተግባራዊ ሳያደርጉ ቀርተዋል ሲሉ የአሠራርና የአመራር ዝርክርክነት መኖሩን ያመላከቱት አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ፤ ፕሮጀክቱን በሚመለከት በየጊዜው ለቦርዱ ጥያቄ ይቀርብ እንደነበርና ቦርዱም ገምግሞ ወደ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የግምገማውን ውጤት ሲልክ መቆየቱን አስታውቀዋል።
“የዘርፉ ባለቤት ብንሆንም ተገልለን ነበር፤ ሪፖርትም ከመብራት ኃይል እየወሰድን ጉድለቶቹን እንናገር ” ያሉት
አምባሳደሩ ፤ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከመብራት ኃይል የሚያገኘውን መረጃ ይዞ እንደ ዘርፍ መግለጫ በሚሰጥበት ወቅት ጊዜም ቢሆን፤ “ምን አግብቷችሁ ነው መግለጫ የምትሰጡት?” በማለት በቦርድ ሰብሳቢው(ዶክተር ደብረፂዮን) በኩል ከፍተኛ ቁጣ ይደርስባቸው እንደነበርም አጋልጠዋል።
“በዚህን መሰሉ አሠራር ፕሮጀክቱ ከሕዝብ ፕሮጀክትነቱ ወርዶ የአንድ ግለሰብ ፕሮጀክት ሆኖ ነበር። ይህም የግድቡን ግንባታ ለውድቀት ከመዳረጉ ባለፈ በአገራችን ታሪክ የሚያሳዝን ድርጊት ሆኖ አልፏል” ያሉት አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ፤ በወቅቱ የህዳሴ ግድቡ ሥራና ውሳኔዎች በሰብሳቢው ውሳኔ ሥር ብቻ የወደቁ እንደነበሩ አስታውሰዋል።
በወቅቱ የነበረውን ቦርድ ችግሮች በሚገባ ለማየት አሁን የተቀየረው ቦርድ በአጭር ጊዜ ያመጣውን ለውጥ ማየት አሳማኝና በቂ ነው ያሉት የቀድሞው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፤ ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት ከግለሰብ እጅ ወጥቶ ወደ ሕዝባዊነቱ እንደተመለሰ፣ ከጉዳት አገግሞ፣ የኮንትራት አስተዳደሩም ተለውጦ አስደናቂ ለውጥ በማምጣት ዳግም አገራዊ መንፈስ ሊላበስ ችሏል ሲሉ የነበረውን ዝርፊያና እንዝህላልነት ይፋ አድርገዋል።